የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸውን የለውጥ ስኬቶች በማስቀጠል፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የልማት ሥራዎችን በእጥፍ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ ከተማዋ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ሁለንተናዊ ለውጦች እና በቀጣይ አምስት ዓመታት ሊተገበሩ የታቀዱ የልማት ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በከተማዋ ከተመዘገቡት ስኬቶች መካከል ዋነኛው "የአስተሳሰብ ለውጥ" መሆኑን ጠቅሰው፣ ትናንት በልዩነቶች ሲገፉ እና ሲያከራክሩ የነበሩ ትርክቶች ወደ አብሮነት፣ ወደ ዘላቂ ልማት እና ሰላም በሚያመሩ የጋራ ዕሴቶች መተካታቸውን አንሥተዋል።
የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከሰባት ዓመት በፊት ከነበረበት 2.8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱ፣ የከተማዋን ጎስቋላ ገጽታ በመቀየር ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎችን የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንሥተዋል።
ትምህርት ቤቶችን በማዘመን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ በመመገብ የትውልድ ግንባታ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው።
የሕፃናት መዋያ ቁጥር ከምንም ወደ 1 ሺህ 100 ማደጉ፣ እንዲሁም ለወጣቶች የስፖርት እና የኪነ-ጥበብ ማዕከላት መገንባታቸው የከተማዋን ማኅበራዊ መስተጋብር እንዳጠናከረው ነው የገለጹት።
በለውጡ ሒደት ውስጥ የተለያዩ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ ሕዝቡን ባሳተፈ እና ባልተቋረጠ ውይይት፣ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመን በመገንባት ችግሮቹን መሻገር ተችሏል ብለዋል።
ለቀጣይ 5 ዓመታት የተቀመጠው ግብ፣ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት በማድረግ፣ ባለፉት ዓመታት የተሠሩ የልማት ሥራዎችን በእጥፍ ማሳደግ እና የነዋሪዎችን ጥያቄዎች በላቀ ሁኔታ መመለስ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: