የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ማኅበራዊ መዋቅር ከ80 በላይ ቋንቋዎች፣ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተጣመሩበት ልዩ የኅብር ውጤት ነው።
ይህ ብዝኃነት የልዩነት እና የመራራቅ ምንጭ ሳይሆን፣ ጥበበኛ ሸማኔ እንደሠራው ድንቅ ጥበብ ወይም ታላቅ ሰዓሊ እንደሳለው ሥዕል ውብ እና ጥልቅ ትርጉም ያለው ብሔራዊ ውህደት ነው።
የክርስትና፣ የእስልምና፣ የይሁዲ እና የሀገር በቀል እምነቶች ተከታዮች ለዘመናት በፍቅር አብረው መኖራቸው የዚህ ማኅበራዊ አብሮነት ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ይህ ታሪካዊ እና ባህላዊ ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃም ዕውቅና አግኝቷል። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቻችንን በዓለም ቅርስነት መዝግቧል።
ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እስከ ጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር፤ ከመስቀል ደመራ፣ ፊቼ ጨምበላላ፣ ገዳ ሥርዓት፣ ጥምቀት እስከ ሸዋል ኢድ በዓላት ድረስ ያሉት ሀብቶቻችን የብዝኃነት ውበት ወደ ብሔራዊ አንድነት ጥንካሬ የተቀየረባቸው መሠረቶቻችን ናቸው።
የኢትዮጵያ ታሪክ በግልጽ እንደሚያስረዳው ሕዝቦቿ በኅብረት ሲቆሙ የውጭ ወረራዎችን በመመከት ታላላቅ ድሎችን አስመዝግበዋል። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የተጎናጸፍነው የዓድዋ ድል ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።
የጣሊያን ወራሪ ኃይል ሉዓላዊነታችንን ለመጣስ ባደረገው ሙከራ፣ ኢትዮጵያውያን በብሔር ወይም በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ በአንድነት ዘምተው ነፃነታቸውን አስከብረዋል፤ ለመላው ጥቁር ሕዝቦችም የፀረ-ቅኝ ግዛት የነፃነት ተምሳሌት ሆነዋል።
በተቃራኒው በኅብረት እና በአንድነት መሠረት ላይ ጥያቄዎች በተነሱባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች ሁሉ ለከባድ መዋቅራዊ እና ማኅበራዊ ፈተናዎች ተጋልጠናል።
እጅግ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት እና ለም መሬት እያለን በውስጥ አለመረጋጋት እና በተቋማዊ አቅም ማነስ ምክንያት ለድርቅ እና ለረሃብ የተጋለጥንባቸው ዘመናት የኅብረት መላላት ያመጣቸው እዳዎች ናቸው።
ከታሪክ በመማር የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከተተገበረው የመደመር እሳቤ መነሻነት፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የማክሮ-ኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የተሠራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው።
ቀደም ሲል ለስንዴ ፍጆታ ማሟያ በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት፣ በቆላማ አካባቢዎች የመስኖ ስንዴ ልማት እና የክላስተር እርሻ በሰፊው ተተግብሯል።
በዚህም በስንዴ አምራችነት በአፍሪካ የቀዳሚነቱን ስፍራ ከመያዝ ባለፈ፣ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ተችሏል። በዚህ ታላቅ ስኬትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት (FAO) የ'አግሪኮላ' ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ትውልድ ተሻጋሪ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለው በኢኮኖሚው ላይ የራሳቸውን አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ ጀምረዋል።
በሌላ በኩል ለዘመናት የተከማቹ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እና ብሔራዊ መግባባትን ለመገንባት አቃፊ ተቋማዊ አሠራሮች ወደ ትግበራ ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ከ93 በላይ አካባቢዎች ሕዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ፣ አጀንዳዎችን በመለየት፣ 4ሺህ ተመካካሪዎችን ያሳተፈ ዋናውን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል።
በተለይም ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የተወሰነው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ ያለፉ በደሎችን እውነት ላይ ተመሥርቶ ማውጣት፣ የካሳ እና የተጎጂዎች ማቋቋሚያ ሥራዎችን መሥራት እና ሀገራዊ እርቅን ማውረድ የሚያስችሉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ዘርግቷል።
ከታሪክ የምንማረው ሀቅ ቢኖር በኅብር ስንቆም የማንገፋ ኃይል፣ ስንበታተን ደግሞ ለፈተና ተጋላጭ መሆናችንን ነው።
የኅብር ቀንን ስናስብ ይህንን የብዝኃነት ውበት ወደ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና እና ዘላቂ ሰላም የመቀየር ኃላፊነት የሁላችንም መሆኑን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: