በከተሞች እየተስፋፋ የመጣው የአረንጓዴ ልማት ሥራ፣ በአየር ብክለት ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በሳይንሳዊ የስጋት ትንበያዎች በመለየት፣ ወደ ተጨባጭ የሕብረተሰብ ጤና እና የሥነ-ምግብ መፍትሔዎች ለመቀየር የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችን ይፋ እያደረገ ይገኛል።
በኢንስቲትዩቱ እየተካሄደ ባለው ሳይንሳዊ ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከሕብረተሰብ ጤና እና ከምግብ ዋስትና ጋር ያለውን ተዛምዶ እየተዳሰሰ ነው።
በጉባኤው የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው፣ በአፍሪካ በየዓመቱ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች በአየር ብክለት ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል እስከ 1 ሺህ 600 የሚደርሱት ኢትዮጵያውያን ህጻናት ናቸው።
በከተሞች እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ ልማት ይህን የጤና ስጋት በመቀነስ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል።
ባለፉት 5 ዓመታት በከተሞች በተከናወነ የኮሪደር ልማት፣ የመንገድ ማስፋፋት፣ የእግር ጉዞን ባህል የማድረግ፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን የማልማት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የማስተዋወቅ ሥራ የአየር ብክለትን በ3.05 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ በጥናት ተረጋጧግል።
የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንቲስቱ ደሳለኝ መሠረት (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በከተሞች የሚገኙ አረንጓዴ ስፍራዎች በ10 በመቶ ቢስፋፉ፣ የሙቀት መጠንን ከ41 እስከ 49 በመቶ እንዲሁም የአየር ብክለትን በ35 በመቶ መቀነስ ይቻላል።
ይህም የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎችን ከ10 እስከ 16 በመቶ በመቀነስ የሞት ምጣኔን ከ5 እስከ 12 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የሚያስችል ፋይዳ እንዳለው በጥናቱ ተመላክቷል።
በሜሮን ምትኩ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: