Search

ምድር በአደይ አበባ ስትደምቅ፣ ኢትዮጵያም በልጆቿ ኅብረት ታሸበርቃለች

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 19

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት በልዩ ሁኔታ የራሷ የሆነ የዘመን መለኪያ ቀመር ያላት ጥንታዊት ሀገር ናት።

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) ከተፈጥሮ ዑደት ጋር ፍጹም የተዋሐደ የዕድሳት ዘመን ነው። እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ያሏቸው 12 ወራት እና እንደ ድልድይ የምታገለግለዋ ባለ 5 (ወይም 6) ቀናት የጳጉሜን ወር የሀገራችንን የዘመን ቀመር ልዩ እና የራሳችን ጥበብ ያደርጉታል።

የመስከረም አየር ሲነፍስ እና የክረምቱ ኃይል በርዶ ተፈጥሮ መልኩን ሲቀይር፣ ሜዳዎች በደማቁ ቢጫ ቀለም በአደይ አበባ ይዋባሉ። ይህ የዘመን አቆጣጠራችን ከዓለም የተለየ የሚያደርገው ታላቅ ተፈጥሯዊ ክስተት መካከል የሚከተሉትን ምስጢሮች መጥቀስ ይቻላል፦

የጨለማው ማብቂያ፦ የክረምቱ ጭጋግ እና ደመና ተገፍፎ፣ ብሩህ ፀሐይ የምትወጣበት የተስፋ ወቅት መሆኑ፤

የተፈጥሮ ትንሣኤ፦ ምድር አረንጓዴ ካባዋን ለብሳ በአደይ አበባ የምታጌጥበት የልምላሜ እና የተስፋ ጊዜ መሆኑ፤ እንዲሁም

የማኅበራዊ ዕድሳት፦ የዘመን መለወጫው ቂም የሚረሳበት፣ ዕርቅ የሚወርድበት እና አዲስ ሀገራዊ ራዕይ የሚሰነቅበት ወቅት መሆኑ ነው።

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ትንሣኤ ልክ እንደ አደይ አበባው አብቦ፣ በልማት ክንዶች ተሣሥሮ፣ በሕዝብ እና በመንግሥት የጋራ ርብርብ በድምቀት እየተፋጠነ ይገኛል።

የዘመን መለወጫ በዓል ሲቃረብ ከተሞቻችን እና የገጠር አካባቢዎቻችን የሚለብሱት አዲስ መልክ የዚሁ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት ሕያው ማሳያ ነው።

ከምሽት የመብራት ድምቀት እስከ ንጋት የጽዳት ንቅናቄዎች እንዲሁም አረንጓዴ ፓርኮችን እውን ከማድረግ አኳያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች፣ የዘመኑ የሽግግር መንፈስ አካል ናቸው።

የጳጉሜን ቀናት በአሮጌው እና በአዲሱን ዓመት መካከል ድልድይ እንደሚሆኑት ሁሉ፣ አሁን እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችም ሀገራችንን ወደተሻለ የብልጽግና ምዕራፍ እያሸጋገሯት ይገኛሉ።

አደይ አበባ ያለማንም አስገዳጅነት ጊዜዋን ጠብቃ መጥታ ምድርን እንደምታስጌጣት ሁሉ፣ ዛሬ ኢትዮጵያውያንም በፈቃዳቸው በየመስኩ በሚያከናውኑት የልማት ርብርብ የሀገራቸውን ከፍታ እያበሰሩ ነው።

ይህም የኢትዮጵያ ዕድገት እና ትንሣኤ ከውጭ የሚመጣ ሳይሆን፣ ልክ እንደ ዘመን አቆጣጠራችን ከራሳችን ጥበብ፣ ጸጋ እና የውስጥ አቅም የሚመነጭ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

የአዲሱ ዓመት መግቢያ የኢትዮጵያ ብልጽግና እንደ አደይ አበባ በሁሉን አቀፍ መልኩ የሚፈነጥቅበት ታላቅ የድል ምዕራፍ ነው!

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: