Search

ከደም ዋጋ እስከ ነጭ ላብ

ረቡዕ ጳጉሜን 04, 2018 23

 ሕብር ለኢትዮጵያውያን የማንነታቸው መገለጫ ዓርማ ነው፡፡ የልዩነት፣ የግጭት እና የመራራቅ ምክንያት ሳይሆን ልክ እንደ ቀስተ-ደመና ቀለማት ተደምሮ ታላቅ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ጥንካሬ የሚፈጥር ጸጋ ነው።

ኢትዮጵያዊነት የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች እና እምነቶች ተዋህደው የሚፈጥሩት ውብ የኅብር ስፌት በመሆኑ፣ ይኸው ብዝኃነታችን፣ የውበታችን እና የጥንካሬያችን ምንጭ ነው።

የቀደሙት አባቶቻችን በብሔር፣ በሃይማኖት ወይም በቋንቋ ሳይከፋፈሉ፣ ልዩነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ በማድረግ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት እና ነጻነት አስከብረዋል።

ለዚህ ትውልድም ኅብር የግጭት መንስኤ ሳይሆን ዋና የጽናት እና የዕድገት አቅሙ ነው።

ለዓድዋ ድል መገኘት በፈሰሰው የአባቶቻችን ቀይ ደም የነጻነት ታሪክ እንደተጻፈ ሁሉ፣ ይህ ትውልድ ደግሞ በነጭ ላቡ የኢትዮጵያን የብልጽግና ታሪክ መጻፍ ጀምሯል።

በቀደመው ዘመን ሀገርን የወረረ ጠላት በጋራ ክንድ እንደተመከተ ሁሉ፣ ዛሬም የትውልዱ ዋነኛ ጠላት የሆነው ድህነት በኅብረት አቅም መቃብሩ እየተቆፈረ ይገኛል።

ሀገራችን እያካሄደችው ያለው የልማት እና የግብርና አብዮት የዚህ አዲስ ምዕራፍ ማሳያ ነው።

በመስኖ ስንዴ ልማት፣ በክላስተር እርሻ እና በአረንጓዴ ዐሻራ የተመዘገቡት ስኬቶች እንደሚያረጋግጡት፣ በጋራ ክንድ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይቻላል።

ይህም ቀደም ሲል በረሃብ እና በእርዳታ ፈላጊነት ይታወቅ የነበረውን ስም በስንዴ አምራችነት እና በልማት ባለቤትነት በመተካት የሀገርን መልካም ገጽታ እየገነባ ይገኛል።

በኅብረት ስንቆም ወራሪ ጠላት ይመከታል፣ ድህነት ይባረራል፣ የቀደመ መጥፎ ስምም ይቀየራል።

 ስለዚህ አባቶቻችን በደማቸው ያቆዩልንን የሕብር አቅም በመጠቀም፣ ልዩነቶቻችንን ወደ ዘላቂ ሰላም፣ ጠንካራ ተቋማትና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና መቀየር የሁላችንም ታሪካዊ ኃላፊነት ነው!

በዓይናለም ሃድራ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: