Search

ከአበባ እስከ ዲጂታል መድረክ፤ የእንቁጣጣሽ ዘመናዊ ጉዞ

ዓርብ መስከረም 01, 2019 83

እንቁጣጣሽ የዘመን መለወጥን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ባህል፣ ታሪክ፣ ፍቅር እና አዲስ ተስፋ በአንድነት የሚያስተስር ታላቅ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ኩነት ነው።

ከንግሥተ ሳባ ታሪካዊ መመለስ ጋር ተያይዞ የሚነገረው እና የክረምቱ ጭጋግ አልፎ በዓደይ አበባ ውበት የሚበሰረው ይህ ጥንታዊ በዓል፣ ዘመናት ቢቀያየሩም መሠረታዊ ሕያው እሴቶቹን ሳይለቅቅ ከአዲሱ ዓለም ጋር መጓዙን አጽንቶ ቀጥሏል።

የጊዜ መንጎድ እና የቴክኖሎጂ ዕድገት የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ እና የበዓላት አከባበር መንገድ መቀየሩ አልቀረም።

የቀደመው ትውልድ የአዲስ ዓመት ሰላምታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ በአካል ተገናኝቶ በሚደረግ ጉብኝት እና የእንኳን አደረሳችሁ ውብ ሥነ-ስርዓት የሚገለጽ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ግን ዲጂታል መድረኮች እና የቴሌኮም አማራጮች ርቀትን አሳጥረው የበዓሉን ደስታ በሰከንዶች ውስጥ ለመጋራት አዲስ በር ከፍተዋል።

በተለይም ወጣቶች የእንቁጣጣሽን የበዓል ድባብ በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ እና በተለያዩ የፈጠራ ይዘቶች በማስደገፍ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሀብት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ባህላዊ አልባሳት፣ የበዓል ገበታዎች፣ የመስከረም አበባ ውበት እና የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በዲጂታል መገናኛዎች ሲሰራጩ የኢትዮጵያ የማይጨፈግግ የባህል ቅርስ ከሀገር ወሰን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።

ዘመናዊነት የበዓሉን የማከበሪያ ስልቶች እና መሣሪያዎች ሊቀይር ቢችልም፣ የዕንቁጣጣሽን ጥንታዊ እና መሠረታዊ ህሊናዊ እሴቶች ግን ሊያደበዝዛቸው አይገባም።

በዲጂታል መድረኮች የታገዘው የዛሬው አከባበር መሠረቱ አሁንም ቢሆን አብሮነት፣ መተሳሰብ፣ ዘመድ ወዳጅን መጎብኘት እና የመልካም ዘመን ምኞት ማጋራት ነው።

ስለሆነም ባህልን እና ትውፊትን መጠበቅ ማለት ከዘመናዊነት እና ከቴክኖሎጂ መራቅ አለመሆኑን ተረድቶ፣ የቀደሙ ጠንካራ ማኅበራዊ እሴቶችን ሳይሸረሸሩ በአዳዲስ ዲጂታል መንገዶች ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል።

እንቁጣጣሽ ከትናንት የታሪክ ማኅደር የወረስነውን ሀገራዊ ማንነት አቅፎ፣ የዛሬን የቴክኖሎጂ ዕድገት ተጠቅሞ፣ ወደ ነገ ብሩህ ተስፋ የሚጓዝ ሕያው እና የማይሞት ትውፊት ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: