ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለአዲሱ "የመደመር መንግሥት" መጽሐፋቸው ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ የመደመር ፅንሰ ሐሳብ ከተጀመረ ቆየት ያለ እና መጽሐፍ ሆኖ ለመወለድም ጊዜ የፈጀ መሆኑን በሂደትም ዳብሮ ወደ መንግሥት አቋምነት ያደገ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የመደመር ሐሳብ በተለያየ ደረጃ ሊተገበር የሚችል ሐሳብ ነው፤ ሰው በግሉ፣ በቤተሰቡ አልያም በቡድን የመደመርን ፅንሰ ሐሳብ ተለማምዶ ሊተገብረው እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የመደመርን ፅንሰ ሐሳብ በግላቸው የተለማመዱት እናም በሠሩባቸው ተቋማት የተጠቀሙበት እንዲሁም ፍሬ ያፈሩበት ሐሳብ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፅንሰ ሐሳቡ ወደ መንግሥት ሐሳብነት ያደገው በሂደት መሆኑን ጠቁመው፤ ከግል እና ከውስን የመሥሪያ ቦታዎች አልፎ የመንግሥት አቋም ለመሆን በርከት ያለ ጊዜ እንደወሰደበትም አስታውሰዋል።
የመደመር ፅንሰ ሐሳብ መጽሐፍ ሆኖ ሳይወጣ በብዙ ሥልጠናዎች፣ ውይይቶች፣ ሰነዶችን በማገላበጥ፣ በተጨማሪ ንባቦች እና ምልከታዎች በማድረግ በሂደት ቀመሩ እየዳበረ፣ እያደገ እና እየሰፋ መጥቶ መጽሐፍ ሊሆን መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ሐሳቡን የጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ብዙዎች የሚቀበሉት እና የሚያምኑበት፤ የሚሥሩበት እና የሚጠብቁት የወል ሐሳብ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
መጽሐፉ በውስጡ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ለራሱ ሕልም ትንታኔ የሚፈይዱትን ታሪኮች ይዳስሳል፤ ወደፊት ደግሞ በመራመድ የዓለምን ነገ እንዲሁም የኛን በነገ ውስጥ ያለንን ሚና ይተነትናል።
መጽሐፉን ይበልጥ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ያደረገው ከውጤት እና ከተጨባጭ ልምድ የተቀዳ መሆኑ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
መደመር ንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በሂደት እየዳበረ እና እየጎለበተ የመጣ በድካም የተገኘ ፅንሰ ሐሳብ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የመደመር መንግሥት ከብዙ ድካም በኋላ የተገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ምናልባትም በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ታሪክ መንግሥታት የሚመሩበት ንድፍ እና ሰነድ በግልጽ በዚህ መልክ ተሰንዶ ለሕዝባቸው ያቀረቡበት እንዳልተገኘ አብራርተዋል።
"የመደመር መንግሥት" መንግሥታት ምን አስበው እንዴት እንደሚሠሩ፤ ለሕዝባቸው፣ ለሚከተላቸው ሰው እና ለታሪክ የሚተውት ፈር-ቀዳጅ እና ታሪካዊ ሰነድ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
በናትናኤል ጸጋዬ
#EBC #ebcdotstream #PMAbiy #PMOEthiopia #Medemer #Yemedemermengist