በሕንድ አስተናጋጅነት በኒው ዴልሂ "ባራት ማንዳፓም" የሚካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ፣ የዓለም አቀፉን የጂኦፖለቲካ የኃይል ሚዛን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተጀምሯል።
በሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሰብሳቢነት "ዘላቂነትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ጥንካሬን መገንባት" በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺጂንፒንግ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላዲሚር ፑቲን፣ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይሳተፋሉ።
ሕንድ ከአውሮፓውያኑ ጥር 1 ቀን 2026 የብሪክስ ሊቀመንበርነቱን ከተረከበች በኋላ ትኩረቷን ጥንካሬና መቋቋም፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ፣ ትብብርና የግሎባል ሳውዝ ድምፅ እንዲሁም ዘላቂነት በተባሉ 4 ዋና ዋና አዕማድ ላይ አድርጋለች።
በጉባኤው ላይ የዶላር የበላይነት ጉዳይ፣ የኢራን እና አሜሪካ ውጥረት እንዲሁም የሕንድ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በዋና አጀንዳነት ይወያዩባቸዋል።
በአዲሱ ልማት ባንክ በኩል ከሚፈቀዱ ፋይናንሶች ውስጥ ከ43.5% በላይ የሚሆነው በሀገር ውስጥ ገንዘቦች የሚሸፈን ሲሆን፣ ይህም ከተለምዷዊው አሰራር የተለየ እና ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ግብፅ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኢራን፣ ሩሲያ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ያቀፈው ይህ ስብስብ በአሁኑ ወቅት የዓለምን 49.5% ሕዝብ፣ የዓለም አቀፉን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 40% እና የዓለም አቀፍ ንግድ 26% ድርሻ በመሸፈን የዓለምን ኢኮኖሚያዊ የኃይል ሚዛን ወደ ባለብዙ ማዕከልነት እየቀየረ ይገኛል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: