ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በውይይታቸውም የመከላከያ ትብብርን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ፣ የማዕድን ዘርፍ እንዲሁም ወደ COP32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ትኩረት አድርገው መምከራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
እነዚህ የትብብር መስኮች የተግባር ትብብርን ለማጠናከር እና ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም እንዳላቸውም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ጥልቅ ታሪካዊ ግንኙነት፣ የቆየ የባህል ትስስር እና በሕዝቦቻቸው መካከል ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ቢሆንም፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ብዙ አቅም አሁንም ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በመሆኑም የታሪክ እና የመልካም ፈቃድ ትስስሩን በቴክኖሎጂ፣ በክህሎት፣ በኢንቨስትመንት፣ በዘላቂ ልማት እና በተጠናከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ወደተመሠረተ የበለጠ ታላቅና የጋራ ተጠቃሚነትን ወደሚያረጋግጥ አጋርነት ለመቀየር አሁን ትክክለኛው ጊዜ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: