18ኛው የብሪክስ ጉባኤ በህንድ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
ነገ ከሚጀመረው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ ከ2 ሺህ በላይ የንግድ መሪዎችን ያሰባሰበ የብሪክስ የንግድ መድረክ ዛሬ በኒው ዴልሂ ተካሂዷል።
መድረኩ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፈጠራ እና ዘላቂ ልማት ዙሪያ የብሪክስ አባል ሀገራትን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው።
መድረኩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ጠንካራ የእሴት ሰንሰለት መዘርጋት እና አካታች ልማት ለማምጣት ያለመ ሲሆን፤ በተለይም እያደገ የመጣውን የብሪክስ ኢኮኖሚያዊ አቅም ወደ ተጨባጭ የጋራ ዕድል መቀየርን አጀንዳው አድርጓል።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፣ እያደገ የመጣውን የብሪክስ የኢኮኖሚ አቅም በተመለከተ አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም ባለፉት 20 ዓመታት የዓለም ጠቅላላ ምርት በ2.5 እጥፍ ሲያድግ፣ የብሪክስ ጠቅላላ ምርት ግን በ4.5 እጥፍ ማደጉን ገልጸዋል።
ይህ አኃዝ የብሪክስ ኢኮኖሚ ከዓለም ኢኮኖሚ አንፃር በእጥፍ ገደማ ማደጉን ያሳያል ብለዋል።
አያይዘውም፣ ይህ የብሪክስ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ለዓለም አቀፍ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማፈላለግ መዋል እንዳለበት አመላክተዋል።
በብሪክስ አባል ሀገራት በተለይ ለፈጠራ አዳዲስ ዕድሎች እየተስፋፉ መሆኑን እና አባል ሀገራቱም የፈጠራና ቴክኖሎጂ ማዕከል እየሆኑ መምጣታቸውን አክለዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: