የሕንድ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ፒዩሽ ጎያል የብሪክስ የንግድ መድረክ በዛሬው ዕለት በኒው ዴልሂ በይፋ ከፍተዋል።
ሚኒስትሩ መድረኩን በከፈቱበት ወቅት፣ ከ2 ሺህ በላይ የንግድ መሪዎች፣ የአባል እና የአጋር ሀገራት ልዑካን የተሳተፉበት ይህ ጉባኤ "በብሪክስ ታሪክ እስካሁን ከተካሄዱት የንግድ መድረኮች ሁሉ እጅግ ግዙፉ ነው" ብለዋል።
በዋናነት ነገ እና ከነገ በስቲያ (ቅዳሜ እና እሑድ) በሚካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብሎ በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የኢራኑ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን እንዲሁም የአስተናጋጇ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጨምሮ ታላላቅ የዓለም መሪዎች ታድመዋል።
18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ፣ ‘ለጽናት፣ ለፈጠራ፣ ለትብብር እና ለዘላቂነት መገንባት' በሚል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል። በዚህም ሰብዓዊነትን ያስቀደመ እና ሰውን ማዕከል ያደረገ አቀራረብን በማራመድ፣ የደቡቡ ክፍለ ዓለም ሀገራትን ትብብር እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ይበልጥ ለማሳደግ ጽኑ አቋም ይዟል።
የዘንድሮው ጉባኤ፣ ሕንድ 11 መደበኛ አባላትን እና በ2025 የተቀላቀሉ 10 አጋር ሀገራትን አቅፎ በቅርቡ የተስፋፋውን የብሪክስ ስብስብ ስትመራ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ታሪካዊ ትርጉም ተሰጥቶታል።
እ.አ.አ በ2009 በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና ተመስርቶ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ደቡብ አፍሪካን፣ በ2024 እና በ2025 ደግሞ ኢትዮጵያን ተጨማሪ አዳዲስ ሀገራትን በማካተት አቅሙን ያሳደገው ብሪክስ፤ አሁን ላይ 40 በመቶ የዓለምን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) እና ከዓለም ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉን የያዘ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ የኢኮኖሚ ስብስብ ለመሆን በቅቷል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: