ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግስት መፅሐፍ ዙሪያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ኢትዮጵያን ሦስት ዓይነት አጥሮች ከዕድገት ጎዳና ነጥለዋት እንደኖሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከዓለም ነጥለው ከቆዩ ጉዳዮች አንዱ አካላዊ አጥር እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ዓለም አዲስ ነገር ፍለጋ ለመለየት ሲታትር ድንበራችንን ዘግተን እርስ በእርስ ስንዋጋ መኖራችን አንዱ የእድገት ማነቆ ሆኖ መቆየቱንም ነው የገለፁት።
ከውጭ እንዳንማር፤ ያለንንም ለውጭ እንዳናሳይ የተከለለ ነገር በመሆኑ ሀብታችንም እሳቤዎቻችንም ውስን እንዲሆኑ አድርጓልም ነው ያሉት።
ሁለተኛው የልማት እና ብልፅግና እንቅፋት የነበረው ተቋማዊ አጥር መሆኑን አንስተው፤ የፊውዳል ሥርዓት ለረጅም ጊዜ የቆየባት ኢትዮጵያ በፖለቲካ እይታ ወደፊት እንዳትራመድ መንገዱን ወግቶ ቆይቷል ብለዋል።
ይህም ስልጣንን በኃይል የመቆጣጠር ልምምድን በሀገሪቱ የፈጠረ እና በኢንዱስትሪ ዘርፉም ከዓለም ኃላ እንድንቀር ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ የሀገር ተቋማት በጥቂት አካባቢዎች የተወሰኑ እና ጥቂት የሰው ኃይል ሆነው የቆዩ እንዲሆኑ አድርጎ ያቆየ መሆኑን አስታውሰዋል።
ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ የተቋማት አገልግሎት በሰው ኃይል በተደራሽነት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ የሚታይ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
ሦስተኛው ከእድገት ከልሎን የቆየው ባሕላዊ አጥር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባሕላችን ለውጥን የማያበረታታ እና አዲስ ነገርን የሚያርቅ ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል።
የኛ እሳቤዎችም ወደ ውጭ ወጥተው እንዲፈተሹ ዕድሉን አልሰጠንም ሲሉ ጠቅሰዋል።
ያለንን አቅም ሳናሳይ ለረጅም ጊዜ ማንቀላፋታችን፤ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ከዓለም በብዙ እርቀት ኋላ እንድንቀር አድርጎናልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በርካታ ሀገራት መሰል ተግዳሮቶች ገጥመዋቸው እንደነበርም አንስተው፤ ነገር ግን ተቋማዊ፣ አካላዊ እና ባሕላዊ አጥሮችን በማስወገድ ዛሬ በስልጣኔ ጎዳና ከፊት መሰለፋቸውንም ጠቁመዋል።
በሰለሞን ከበደ
#EBC #ebcdotstream #PMAbiy #PMOEthiopia #Medemer #Yemedemermengist