Search

ወጣቶች መሪነትን ከአሁኑ አስበው መትጋት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ነሐሴ 14, 2017 163

መሪነት በረጅም የጊዜ ሂደት ውስጥ የሚመጣ እና እየዳበረ የሚሄድ ጥበብ በመሆኑ ወጣቶች መሪነትን ከአሁኑ አስበው መትጋት አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የመደመር መንግሥት" የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ በተመለከተ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ መሪነት በተጨባጭ እውቀት እና ልምድ ላይ ሊመሰረት ይገባል ብለዋል፡፡

መሪ መሆንን መመኘት ይቻላል ለዚህም ከፍተኛ ስራ ይጠይቃል ነገር ግን ይህ መሻት ባዶ መሻት እንዳይሆን በተጨባጭ እውቀት እና ልምድ ላይ ሊመሰረት ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

እከሌ መሪ ሆኗል እኔም መሪ እሆናለው ማለት ባዶ መሻት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አማራጭ ሀሳብ ይዞ በመቅረብ በተጨባጭ ፖሊሲ እና በሀሳብ የበላይነት የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የተሰሩ ስራዎችን በማጣጣል ብቻ መሪነት የሚያስቡ ካሉ ይህ የማይቻል መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያን መምራት ማለት ከአፍሪካ ሁለተኛ ከዓለም ደግሞ አስረኛ የሕዝብ ቁጥር ያለውን ሀገር መምራት ነው፤ ይህንን ሀገር ለመምራት ራስን ቀድሞ ማብቃት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ወጣቶች መሪነትን ከአሁኑ አስበው መትጋት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ማድረግ ከተቻለ የማይቻል ነገር አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ

#EBC #ebcdotstream #PMAbiy #PMOEthiopia #Medemer #Yemedemermengist