ኢትዮጵያ እጅግ ውድ እና ለኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ የብረት፣ የከበሩ ድንጋዮች እና የኢንዱስትሪ ማዕድናት በመያዝ የታደለች ሀገር ብትሆንም፣ አብዛኛው የማዕድን ሀብት ገና ወደ ልማት አልተሸጋገረም።
ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት የማዕድን ዘርፉን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ በማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም አሁን ላይ ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጣቸው ማዕድናት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ለአብነትም ፖታሽ ብንመለከት በአፋር ክልል ዳሎል ሰፊ እና እጅግ ግዙፍ የሆነ የፖታሽ ክምችት ይገኛል። በአካባቢውም ከ11 እስከ 12 ቢሊዮን ቶን የሚደርስ ግዙፍ የፖታሽ (ጨው) ክምችት እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል።
የማዕድን ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአፋር ክልል ዳሉል ወረዳ በሚገኝ 365 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የፖታሽ ማዕድን ማውጫ ቦታ ላይ ማዕድኑን የማውጣት ፈቃድ ሰጥቷል።
በዚህም ለረጅም ዓመታት ሲነገርበት የቆየው የኢትዮጵያ የፖታሽ ሀብት ከወረቀት አልፎ ወደ ተጨባጭ የልማት ምዕራፍ እንዲገባ በመንግሥት በኩል ጠንካራ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በውስጧ ከያዘቻቸው እጅግ ሰፊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከሆኑ ማዕድናት አንዱ የሆነው ፖታሽ፣ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እውን ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ይህ ማዕድን ለግብርና ማዳበሪያ ማምረቻነት ከፍተኛ ግብዓት ነው። በመሆኑም ሀገራችን ለግብርናው ዘርፍ እንቅፋት የሆነባትን የማዳበሪያ እጥረት ለመቅረፍ አቅም ይሆነዋል፡፡
ፖታሽ በዋነኛነት ለሰብል ልማት እና ለምነት ማሻሻያ የሚያገለግል የኬሚካል ማዳበሪያ ዋና ግብዓት በመሆኑ፣ ሀገራችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ያግዛል።
በመሆኑም ማዕድኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ገብቶ ለዓለም ገበያ መቅረብ ሲጀምር ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ዕድገት ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል።
የኢንዱስትሪው መስፋፋት ለብዙኃን ዜጎች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል በመፍጠር አካባቢያዊ ልማትን ከማፋጠን አንጻርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: