Search

የጊፋታ ገበያዎች፤ ‘ሀረ ሀይቆ’፣ ‘ቦቦዳ’ እና ‘ጎሻ’

ሓሙስ መስከረም 07, 2019 45

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት የተመዘገበው የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" ሲቃረብ የወላይታ ምድር በባህላዊ እሴቶች፣ በደስታ እና በልዩ የሸመታ ድምቀት ይሞላል።

ከዓመት እስከ ዓመት በጉጉት የሚጠበቀው ይህ ታላቅ በዓል መቃረቡን የሚያበስሩት ደግሞ በተለየ የሕዝብ እንቅስቃሴ እና ባህላዊ ሁነቶች የሚታወቁት ሦስቱ ልዩ ገበያዎች ናቸው።

እነዚህ ሦስት ገበያዎች በበዓሉ ዋዜማ የሚከወኑ እና እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ልዩ ባህሪያት እና ትርጉም ያላቸው ሁነኛ የሸመታ ስፍራዎች ናቸው።

የመጀመሪያው ሀረ ሀይቆ ገበያ ነው። "ሀረ ሀይቆ" ማለት በጥሬ ትርጉሙ "አህያ የሚሰቃይበት" እንደማለት ሲሆን፤ በዓሉን አስመልክቶ ኅብረተሰቡ ለጊፋታ የሚያስፈልጉትን የተለያዩ የምግብ፣ የጌጣጌጥና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ከየአካባቢው አዘጋጅቶ የሚያቀርብበት ነው።

በመሆኑም አህዮች ከወትሮው በተለየ መልኩ ከፍተኛ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡበት እና የሚደክሙበት ገበያ በመሆኑ ይህን ስያሜ አግኝቷል።

ሁለተኛው ቦቦዳ ገበያ ተብሎ ይጠራል። ከጊፋታ በዓል መግባት በኋላ ማኅበረሰቡ ለረጅም ቀናት እረፍት የሚያደርግ በመሆኑ ቀጣይ ገበያዎች በቅርብ ቀናት ውስጥ አይካሄዱም።

በዚህም የተነሳ ሕዝቡ ለዚህ የእረፍት ጊዜ የሚበቃውን ሙሉ የቤት ፍጆታ በአንድ ጊዜ አከማችቶ ለመሸመት የሚረባረብበት ገበያ ነው።

በዚሁ ምክንያት ገበያው ከፍተኛ ጥድፊያ፣ የእሽቅድድም አየር እና የደራ የሸመታ ፍላጎት የሚታይበት በመሆኑ "ቦቦዳ" ተብሎ ይጠራል።

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ጎሻ ገበያ ነው። "ጎሻ" ማለት በብሔሩ ቋንቋ "እብደት" የሚል አቻ ትርጉም አለው።

ከጎሻ ገበያ ቀጥሎ በዓሉ ስለሚገባ ሌላ ተጨማሪ ገበያ አይኖርም። በመሆኑም ሕዝቡ "ምን ቀረብኝ? ምንስ ጎደለብኝ?" በሚል ጭንቀትና ስጋት ገና በጠዋት ወደ ገበያ በመውጣት ዕቃዎችን ሲሸምት፣ ሲደራደርና ሲመላለስ ይውላል። ይህ ሂደት ከፍተኛ ትርምስምስ ያለ አየር ስለሚፈጥር ገበያው በዚሁ ስም ይጠራል።

በዚህ ዓመትም እነዚህ ሦስቱ ባህላዊ ገበያዎች የጊፋታን በዓል ልዩ ድምቀትና ባህላዊ ውበት በግልጽ እያሳዩ ይገኛሉ።

የዘንድሮው የጊፋታ በዓል የትውልድ ቅርስን እንጠብቅ፣ የጊፋታን ውርስ እናስቀጥል በሚል መሪ ቃል መስከረም 10 ቀን 2019 . በድምቀት ይከበራል።

በትዕግስቱ ቡቼ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: