Search

ፈተናዎችን ወደ ድል የቀየሩ የዕድገት ምዕራፎች

ሓሙስ መስከረም 07, 2019 37

የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ በወረቀት ላይ በሰፈረ ዕቅድ ብቻ ሳይወሰን ወደ መሬት በወረዱ ተጨባጭ ሥራዎች እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በሚቀይሩ ውጤቶች እየተመዘነ ይገኛል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የልማት መስኮች የተከናወኑ ግዙፍ ሥራዎች የዚህ ጽኑ ጥረት ሕያው ምስክሮች ናቸው።

ሀገራችን ከባድ የኢኮኖሚ ጫናዎችን፣ የዓለም አቀፍ ቀውሶችን እና የውስጥ ፈተናዎችን በጽናት ስትጋፈጥ መቆየቷ አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ እነዚህ ፈተናዎች የልማት ጉዞውን ከማስቆም ይልቅ የተሻለ የመቋቋም አቅም እንድትገነባ አድርገዋታል።

በዚህም መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ጀምሮ የምግብ ዋስትናን እስከ ማረጋገጥ እና የዲጂታል ኢኮኖሚን እስከ መገንባት የሚደርሱ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

የከተማ ኮሪደር ልማት እና አዳዲስ የፍጥነት መንገዶች ግንባታ የከተሞችን ገጽታ በዘመናዊ መንገድ ከመቀየር ባሻገር የንግድ እና የትራንስፖርት ፍሰትን በእጅጉ አሳልጠዋል።

በሌላ በኩል ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተከናወኑ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለኢንዱስትሪ፣ ለግብርና እና ለቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀርባ አጥንት የሆነውን የኃይል አቅርቦት በአስተማማኝ ሁኔታ እያሳደጉት ይገኛሉ።

በግብርናው መስክ የተመዘገበው ለውጥ የኢኮኖሚው ዋነኛ ሞተር ሆኗል።

በተለይም ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ሀገራዊ ስኬት እንዲሁም 'ሌማት ትሩፋት' መርሐግብር የተገኙ የሥጋ፣ የወተት እና የማር ምርት ዕድገቶች ግብርናው ከተለምዷዊ አሠራር ወደ ገበያ ተኮር እሴት ፈጠራ መሸጋገሩን ያረጋግጣሉ።

ይህም ምርታማነትን ከማሳደግ አልፎ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል ትልቅ መሠረት ጥሏል።

ይህንን የግብርና ግብዓት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ደግሞ 'ኢትዮጵያ ታምርት' በሚል ንቅናቄ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተነቃቃ ነው።

የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ የተዘጉ ፋብሪካዎችን መልሶ በማንቀሳቀስ እና አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ ከጥሬ እቃ ወደ እሴት ፈጠራ የሚደረገው ሽግግር የውጭ ገበያ ተወዳዳሪነትን በእጅጉ አጠናክሯል።

በተመሳሳይ 'ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030' ስትራቴጂ ትግበራ ፈጣን የኢኮኖሚና የአገልግሎት አሰጣጥ አብዮት እየፈጠረ ነው።

እንደ ቴሌ ብር ያሉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች፣ ብሔራዊ መታወቂያ እና የኢ-አገልግሎቶች መስፋፋት የዜጎችን እንግልት ከማስቀረት ባለፈ ለወጣቶች እና ለግሉ ዘርፍ ሰፊ የፈጠራ ሥራ ዕድሎችን ከፍተዋል።

እነዚህ ስኬቶች በየዘርፉ የተነጣጠሉ ሳይሆኑ ምርትን፣ ገበያን፣ መሠረተ ልማትን እና ቴክኖሎጂን በአንድ ላይ በማስተሳሰር ጠንካራ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች ናቸው።

የአምስት ዓመቱ ጉዞ ከተገኙት ድሎች ይልቅ በቀጣይ ለሚሠሩ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አቅም የፈጠረ ምዕራፍ ሆኖ አልፏል።

ያለፉትን ስኬቶች ይበልጥ ማጠናከር፣ የታዩ ክፍተቶችን በውጤታማ አሠራር መሙላት እና አዳዲስ ዕድሎችን ወደ ላቀ ሀብትነት መቀየር የቀጣዩ የልማት ጉዟችን ማዕከላዊ ትኩረት ይሆናል።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: