Search

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ያደረገው ተሳትፎ ውጤታማ መሆኑን ገለጸ

ረቡዕ መስከረም 06, 2019 110

የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ አብዲከሪም ሼክ ሙሴ (ቀልቢደጋህ) እንደተናገሩት፣ በሀገራችን የተጠራቀሙ መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት የተጀመረው አገራዊ ምክክር ወሳኝ እና አካታች እንደነበር አስታውቀዋል።

ድርጅታቸውም የሶማሊ ማኅበረሰብን መሠረታዊ አጀንዳዎች ይዞ በመቅረብ በሂደቱ ላይ ጥልቅና ንቁ ተሳትፎ ማድረጉን አረጋግጠዋል።

ድርጅታቸው ሰላምን ለማደፍረስና ሕዝብን ለማያባራ መከራና ስቃይ ሊዳርግ ቆርጦ የተነሳን ኃይል በፅናት እንደሚታገልም አስታውቋል።

ይህ እኩይ ተግባር ለበርካታ አመታት የሶማሊ ክልልን ህዝብ ለከፋ ችግር እና ለውርደት ሲያጋልጥ የነበረው የህወሃት ቡድን ተግባር ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህንንም ለመመከት ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በመሆን ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንደሚወጡ ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በቀረበው የሰላም ጥሪ ግንባሩ የትጥቅ ትግሉን ማቆሙንና በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ 7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ በመሳተፍ የምክርቤት መቀመጫዎችን ማሸነፍ መቻላቸውን አብዱልከሪም ሼህ ሙሴ ተናግረዋል።

ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጭን መከተላቸው የሶማሊ ሕዝብን የዘመናት ጥያቄዎች የሚመልሱ በርካታ ታሪካዊ ስኬቶችን እንዲያስመዘግቡ እድል የፈጠረ መሆኑንም አክለዋል።

ክልሉ በትጥቅ ትግል ወቅት ከነበረበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመውጣት አስደናቂ ዕድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በመሆኑም የተገኘው ሰላም ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግንባሩ ፅኑ ፍላጎት እንዳለውና ለውጤታማነቱም ኦብነግ ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ ከለውጡ በፊት በክልሉ የነበረውን አለመረጋጋት በመምራት የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንዲቀጠፍና ክልሉ ከፍተኛ ኪሳራ ላይ እንዲወድቅ ያደረጉ የሕወኃት ቡድን አመራሮች አሁንም የፀጥታ ችግር ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑ ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።

ሕዝብን ወደ ቀደመው መከራ ለመመለስ የሚደረገው የጥፋት ኃይል ጥረት በጭራሽ እንደማይሳካና በክልሉ ላይ ጥፋትና ውድመት ያደረሱ አካላትን ግንባሩ በሕግ እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።

 

በመጨረሻም በአንዳንድ የመረጃ ምንጮች "የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር 'ጽምዶ' ከተሰኘው አፍራሽ ቡድን ጋር ሕብረት ፈጥሯል" ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ፍፁም ሐሰትና ድርጅቱን የማይወክል ነው ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: