Search

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አራተኛው መጽሐፍ - “የመደመር መንግሥት” የያዘቸው ቁምነገሮች

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 1262

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የመደመር መንግሥት” የተሰኘው አራተኛ መጽሐፋቸውን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በዘመናዊት ኢትዮጵያ ያሉት መንግሥታት የመንግሥታቸውን ቅርፅ፣ እሳቤ እና አደራረግ ሰንደው አስቀምጠው አያውቁም።

ምናልባትም በአፍሪካ ደረጃም በእንደዚህ ዓይነት መልክ መንግሥታቸው ያለው እሳቤ፣ የአተገባበር ሥልቱን፣ የሚከውንበትን መንገድ፣ ሊያሳካ የሚያስበውን ግብ እና ውጤት በዝርዝር ያስቀመጠ፣ ለሕዝቡም የገለጠ መንግሥት የለም።

እናም ይህ በራሱ “የመደመር መንግሥት” የተሰኘውን ሰነድ ፈር ቀዳጅ ያደርገዋል።

የመደመር መንግሥት ዋና ሐሳቡ ግን በፅንስ (በንድፍ) እና በፍልስፍና ያየነውን፣ ታሪኩን ጉዞውን ያወቅነውን፣ ትውልድ እንዴት እንደሚሠራ ያስቀመጠው መደመር ተቋማዊ ቅርፅ እንዲይዝ ማድረጉ ነው።

መደመር መንግሥታዊ ቅርፅ እንዲይዝ የሚያደርገው ይህ ሰነድ እንደሆነ እና ከግል እና ከቡድን ወጥቶ እንደመንግሥት እሳቤው እንዴት እንደሚሠራ በዝርዝር እንደሚያስቀምጥም ገልጸዋል።

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚታየው አንደኛው ጉዳይ “እኛ እና የተቀረው ዓለም የተላለፍነው የት ነው?” ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ስብራቶቻችን የት ጀመሩ? የሚለውን እና ያንን ከዓለም የለየንን ጉዳይ በዝርዝር ማንሣቱ ነው።

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኋላ ለመቅረታችን ምክንያት የሆኑ ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን በዝርዝር ማተቱ ነው።

በተጨማሪም፤ በእኛ እና በዓለም መካከል የተፈጠረውን ክፍተት፤ እንዴት ልናጠብበው እንችላለን? ምን ዓይነት መደመራዊ አካሄድ ብንከተል ክፍተቱ ሊጠብብ እንደሚችል ደግሞ ይተነትናል።

ታሪኩን ካነሣ እና ክፍተቱን ካየ በኋላም፤ ክፍተቶቹ መጥበብ የሚችሉባቸው መንገዶችንም ያመላክታል።

ያንን ለማድረግም ከተለመደው የመክዳት አካሄድ ተላቅቀን መደመራዊ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና የመስፈንጠር መንገዶችን መከተል እንዳለብን ይመክራል።

ካልፈጠርን፣ ካልፈጠንን በአንዳንዱ ጉዳዮች ደግሞ ካልዘለልን በስተቀር ያንን ልዩነት እያጠበብን መሄድ ያቅተናል ብሎ በዝርዝር ያትታል - የመንደመር መንግሥት መጽሐፍ።

ሐሳቡን ሲዘረዝርም ከቀደሙት መንግሥታት ኀልዮት ጋር ራሱን ያወዳድራል። ለምሳሌ ገበያ መር ካልንበት ጊዜ ጋር ራሱን ያወዳድራል፤ ወይም የእዝ ኢኮኖሚ ባልንባቸው ወቅቶች የነበረውን አሠራር እና አደራረግ ያወዳድራል።

እንዲሁም ልማታዊ መንግሥት ያልንባቸው ጊዜያትም እነዚያን ኀልዮቶችን እንዳለ አይቷቸው፤ አንሥቶ በንፅፅር ለምን ይህኛውን እሳቤ እንደምንከተል ያመላክታል።

መደመርን ፍልስፍናዬ አድርጌ ነው ብልፅግናን የማረጋግጠው የሚል መንግሥት ምን ዓይነት ባሕርያት እንዳሉት በዝርዝር ያስቀምጣል።

ስለሚከተለው ስትራቴጂ፤ ስለሚያስመዘግበው ውጤትም፤ በተጨማሪም በሀገር ውስጥም፣ ከሀገር ውጭም ስለሚኖረው ግንኙነት በዝርዝር ያትታል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የተሻገረ፣ የተለወጠ እና የዘመነ ገጠር እንዴት መፍጠር እንደምንችል በዝርዝር እንደሚያትትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

ዘመናዊ እና የተሳለጠ ከተማ እንዴት መፍጠር እንደምንችል፤ በኢንዱስትሪው፣ በቱሪዝሙ ያሉን ውጤቶች በፈጠነ መንገድ አሰናስሎ ለሀገር ጥቅም እና ዕድገት እንዴት ማዋል እንደሚቻል የመደመር መንግሥት በዝርዝር ያስቀምጣል።

ይህንን ሰነድ በደንብ ጊዜ ወስዶ ያየ ሰው መንግሥት ምን ዓይነት መልክ፣ ፍላጎት፣ አደራረግ እንዳለው ያያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከሆነ ጊዜ በኋላ ተመልሶ ውጤቱን ሲያይ በምን እሳቤ እንደመራነው በግልጽ ሊገነዘብ ይችላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሌላኛው የሚያነሣቸው ሐሳቦች ለስኬታችን ወሳኝ ጉዳዮችን ነው። በተለይም የፖለቲካ ስክነት ለኢኮኖሚ ስምረት እንዲሁም ለተቋም ፍሰት እና ስልጠት የመሆኑን ነገር በዝርዝር ያነሣል ነው ያሉት።

ተግዳሮቶቻችንንም እንዲሁ በደንብ እንደሚያስቀምጥ እና ይህ ጉዳይ እንዳይሳካ ምን ዓይነት ፈተነዎች አሉብን? የሚለውን እንደሚዳስስ ጠቁመዋል።

ከተግዳሮቶቹ አንደኛው ሌብነት ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጊዜም የገንዘብም ሌብነት በከፍተኛ ደረጃ ፈጠራን፣ ፍጥነትን እና መሳካትን የሚያግድ አጥር እንደሆነ መጽሐፉ እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ገበያው ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን እና ፖለቲካ እንደ ሸቀጥ የሚሸቀጥበት ሥርዓት ከሐሳብ የራቀ መሆኑ ያለውን አደጋ መጽሐፉ ያስቀምጣል።

ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለን ምልከታ በጣም የተራራቀ መሆኑን እና አንድ ሀገራዊ ትርክት መፍጠር እስካልቻልን ድረስ ኢትዮጵያን በምንፈልገው ልክ አስቀምጠን ጥቅማችንን ለማስከበር ያለውን ፈተናንም ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንዳሉት መጽሐፉ ችግሮቹን አሳይቶ ብቻ ግን አያልፍም፤ መውጫ መንገዶችንም ያመላክታል።

ለምሳሌ የፖለቲካ ገበያው የሐሳብ ገበያ መሆን እንዳለበት፤ በግል ባለን ጥላቻ፣ ስሜት ሳይሆን በተቋሙ፣ በግለሰቡ፣ በቡድኑ ሐሳብ ላይ መጫወት ይኖርብናል፤ እንደ ሀገርም የጋራ ትርክት መገንባት አለብን የሚል አቋም የተንፀባረቀበት መሆኑን ነው ያብራሩት።

ይህ ማለት ግን እኔ የራሴ የሆነ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ የለኝም ማለት ሳይሆን አብረን በምንኖርበት ቅጥር ውስጥ ሊያሰባስበን የሚችል የወል የሆነ ትርክት መገንባት እንችላለን፤ መሆንም አለበት ነው እንደማለት መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ማኅበራዊ ድልቦቻችን (social capital)፣ የደለበ የኢትዮጵያን ሀብት እየመነዘርን መጠቀም አለብን የሚል እሳቤን እንደያዘ ጠቅሰዋል።

ያንን ስናደርግ እኛ እና ዓለም የት እንደተለያየን ማወቅ፤ ፈተናውን መለየት፤ ፈተናውን የምናጠብበትን ስትራቴጂ መንደፍ፣ የምንጠቀምባቸውን ሥልቶች አንድ በአንድ ማሰናሰል እንደምንችል መጽሐፉ ይተነትናል።

በአጠቃላይ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንዴት ማየት እና ለልጆቻችንም ማውረስ እንደምንችል በዝርዝር የሚያትት፣ ብዙ ቁምነገሮችን በውስጡ የያዘ ሰነድ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በዮናስ በድሉ

#EBC #ebcdotstream #PMAbiy #PMOEthiopia #Medemer #Yemedemermengist