Search

በዓለም እጅግ ልበቀና በመባል የሚታወቁት ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ አረፉ

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 124

በዓለም እጅግ ልበቀና በመባል የሚታወቁት የሮድ አይላንድ ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ88 ዓመታቸው ማረፋቸው ተሰምቷል።

ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በፊታቸው የሚቀርቡትን ሁሉ በእዝነት እና እጅግ ትህትና በተሞላበት መንገድ በማናገር፣ በፍፁም ቅንነት በመዳኘት እና ችግራቸውንም ለመረዳት በሚያደርጉት ጥረታቸው ይታወቃሉ።

እርሳቸው ፊት የቆሙ ሁሉ ታዲያ ፍትሕን እንደሚያገኙ በልበሙሉነት ያምናሉ።

ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተመልካቾች ካባ ከለበሰ ሰው በላይም ነበሩ፤ የደግነት፣ የማስተዋል እና የሰብአዊነት ምልክት የሆኑ ዳኛ ናቸው ሲሉ ብዙዎች ይመሰክራሉ።

በርኅራኄ፣ በትህትና እና በሰዎች መልካምነት ላይ የማያወላውል እምነት የነበራቸው ዳኛ ካፕሪዮ በፍርድ ቤት እና ከዚያም ባሻገር በሠሩት ሥራ የብዙዎችን ሕይወት ነክተዋል።



ሞቅ ባለ ፈገግታቸው፣ በቀልድ አዋቂነታቸው የሚታወሱ ሲሆን ልኬት በሌለው ደግነታቸው መልካም ለዋሉላቸው እና በዚህ መልካም ሥራቸው በተማረኩ ሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ይኖራሉ።

ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በተለይ በቴሌቭዥን በሚተላለፈው የፍርድ ሄደታቸውን በሚያሳየው ፕሮግራማቸው የሚታወቁ ሲሆን የመንገድ ትራፊክ ሕግ በመጣሳቸው ተከሰው በፊታቸው የሚቆሙ ተከሳሾችን በፍፁም አባታዊ ትህትና በማናገር እና ችግሮቻቸውን በመረዳት ያሳዩት በነበረው ርህራሄ እና ፍቅር በብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል።

እኚህ ምስጉን ዳኛ በያዛቸው የጣፊያ ካንሰር ጋር ሲታገሉ ቆይተው በሆስፒታል ውስጥ በቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ በልጆቻቸው እና በልጅ ልጆቻቸው ተከበው በሰላም አርፈዋል።

ከመሞታቸው በፊት ለተከታዮቻቸው በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት የቪዲዮ መልዕክት ለጤናቸው እንዲጸልዩላቸው ጠይቀው ነበር። ከተቆረጠላቸው ቀን ግን ማለፍ አልቻሉም።



በዳኝነት ያገለግሉበት የነበረው ሮድ አይላንድ ፍርድ ቤት ባወጣው የኀዘን መግለጫ፣ “ለእርሳቸው ክብር ሲባል ልክ እርሳቸው ሲያደርጉት እንደኖሩት ሁሉ እያንዳንዳችን ትንሽ ርኅራኄን ወደ ዓለም ለማምጣት እንትጋ” ብሏል።

በዮናስ በድሉ

#EBC #ebcdotstream #JudgeFrankCaprio #humanity