Search

የመስከረም ውበት እና ትውፊት፦ የተስፋ፣ የእርቅ እና የብዝኃነታችን መገለጫ

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 57

ወርሃ መስከረም ተፈጥሮ አዲሱን የመኸር እና የብርሃን ዘመን የምታበስርበት፣ ምድር በዐደይ አበባ የምታሸበርቅበት እና በየአቅጣጫው የተስፋ ወጋገን የሚፈካበት ልዩ ምዕራፍ ነው።

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር መስከረም የዓመት መባቻ ብቻ ሳይሆን፣ የማኅበራዊ እና መንፈሳዊ መታደስ፣ እንዲሁም የይቅርታ እና የእርቅ ጥልቅ ትርጉም ያዘለ ወቅት ነው።

ከባድ ክረምት እና የወንዞች ሙላት አልፎ ሰማዩ ሲጠራ፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ፣ ከፈጣሪው እና ከወንድሙ ጋር ያለው ትሥሥር በጥበብ ይታደሳል።

በዚሁ ወር በተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዘንድ የሚከበሩት የዘመን መለወጫ፣ የምስጋና እና የሃይማኖት በዓላት ኢትዮጵያ ምን ያህል በባህል፣ በቋንቋ እና በጥንታዊ ዕውቀቶች የታደለች የፍቅር እና የውበት ምድር መሆኗን ያረጋግጣሉ።

በመላው የሀገራችን አቅጣጫዎች የሚከበሩት እነዚህ በዓላት የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ የባህል ሕብረ-ቀለም በግልጽ ያሳያሉ።

የኦሮሞ ሕዝብ በጥንታዊው የገዳ ሥርዓት መሠረት ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት እና ለምድር ሰላም የሚጸልይበት ኢሬቻ፣ ከአስቸጋሪው የክረምት ወቅት ወደ አዲሱ ብሩህ ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ነው።

የወላይታ ሕዝብ ኮርማ ጪሻ የተሰኘውን ነጭ አበባ ተፈጥሯዊ ምልክት አድርጎ የሚቀበለው ጊፋታ የነጻነት፣ የደስታ እና የዘመን መለወጫ መገለጫ በመሆን ይደመቃል።

የሀዲያ ብሔር መቻዕል ሜራ ዝግጅት ጀምሮ አታካ እና ምሽት እና በቶሞራ ደመራ የሚያደምቀው ያሆዴ በዓል፣ የወንድማማችነት እና የእርቅ ማብሰሪያ ነው።

ይህ የባሕል ትሥሥር ይበልጥ ደምቆ የሚታየው በዚሁ ወር ከሚከበረው ደማቁ የመስቀል በዓል ጋር ሲዋሃድ ነው።

የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ከባህላዊ ጋር አጣምሮ በመላው ኢትዮጵያ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ ደመራው ሲለኮስ የሚታየው ብርሃን የሰላም እና የአንድነት ተምሳሌት ነው።

ይኸው በዓል በየአካባቢው ካሉ ባህላዊ ዕሴቶች ጋር ተሰናስሎ መከበሩ ውበቱን ይጨምረዋል። በጋሞ ሕዝብ በእንግጫ ዝግጅት ታጅቦ ዱቡሻ ባህላዊ አደባባይ ፍቅርን እና ፍትሕን የሚያነግሠው ማስቃላ፣ በጉራጌ ማኅበረሰብ በክትፎ፣ በአዳብና ጨዋታ እና በዮቃ ዕርቅ የሚደምቀው የመስቀል በዓል የዚሁ ታላቅ ሕብረ-ቀለም አካላት ናቸው።

በተጨማሪም የከምባታ እና ጠምባሮ ሃሹ ማስቃላ የከፋ ማሽቃሮ እና የጎፋ ጋዜ እና ዮኦ ማስቃላ ሁሉ የዚሁ ውብ ኢትዮጵያዊነት ማሳያዎች በመሆን በመላው ሀገራችን ደምቀው ይከበራሉ።

እነዚህ በመስከረም ወር የሚከበሩ ሀገራዊ ትውፊቶች ጥልቅ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አላቸው።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ቅሬታዎችን በመደበኛው የፍርድ ቤት መዋቅር ሳይታጠሩ በጥንታዊ የዕርቅ ሥርዓቶች መፍታት የነዚህ በዓላት ዋነኛ መገለጫ ነው።

የጋሞ ዱቡሻ፣ የኦሮሞ ሰፉ፣ የሀዲያ ያሆዴ ዕርቅ እና የጉራጌ ዮቃ ሥርዓቶች የቆዩ ቂሞችን አጥበው በማስወገድ ዘላቂ ሰላምን ያሰፍናሉ።

በኢኮኖሚ በኩል ደግሞ የመስከረም ወር በንግድ፣ በምግብ አቅርቦት እና በእንስሳት ግብይት የሚያሸበርቅበት፣ አርሶ አደሩ እና ነጋዴው የልፋታቸውን ውጤት የሚያጣጥሙበት ወቅት ነው።

ከዚህም በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማነቃቃት የየአካባቢውን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ይደግፋሉ።

እነዚህ እና በጽሑፉ ውስጥ ያልተጠቀሱት ድንቅ የኢትዮጵያ በዓላት መላው የሀገራችንን ሕዝብ በጽኑ የማኅበራዊ ገመድ ያስተሣሥራሉ። የተለያየ ባህል እና ቋንቋ ያላቸው ዜጎች በየአደባባዩ ተገናኝተው የሌላውን ባሕላዊ ዕሴት እና ውበት በማወቅ የጋራ ባለቤትነታቸውን ያጠናክራሉ።

በዩኔስኮ የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ላይ የሰፈረው የመስቀል በዓልን ጨምሮ ሌሎችም በሒደት ላይ ያሉ ሀብቶች፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን አዎንታዊ ገጽታ እና በፍቅር አብሮ የመኖር ታሪክ በጉልህ ያስተዋውቃሉ።

ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎች እና የዳያስፖራ አባላት በነዚህ በዓላት አማካኝነት የሕዝባችንን እንግዳ ተቀባይነት፣ ሰላም ወዳድነት እና ጥንታዊ የሥልጣኔ ዕሴቶች በዓይናቸው ይመለከታሉ።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እነዚህን የባሕል ሀብቶች ለቱሪዝም ልማት፣ ለሀገራዊ መግባባት እና ለባሕል ዲፕሎማሲ በስፋት እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የኦሮሞውን እሬቻ፣ የወላይታውን ጊፋታ፣ የሀዲያውን ያሆዴ፣ የጋሞውን ማስቃላ እና የጉራጌውን መስቀል የራሱ የባሕል ሀብት አድርጎ ሲቀበል፣ ብዝኃነት ጥንካሬያችን እና መዋቢያችን መሆኑ ይረጋገጣል።

በመስከረም ወር የሚፈካው እያንዳንዱ አደይ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የተስፋ ተምሳሌት ነው።

እነዚህን ትውፊት አዘል ዕሴቶች ጠብቆ ማቆየት እና የጋራ ቤታችንን ሰላም በእርቅ ማጽናት የሁላችንም ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: