Search

ታዳሽ ኃይል፡ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አብዮት መሠረት

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 57

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ሀብት የዕለት ተዕለት የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ የኢንዱስትሪ እና የምርት ሽግግር ዋነኛ ሞተር ነው።

የውኃ፣ የፀሐይ፣ የንፋስ እንዲሁም የጂኦተርማል ኃይል ምንጮችን በማልማት አስተማማኝ መሠረተ ልማት መገንባት ለማምረቻው ዘርፍ ለእሴት ፈጠራ እና ለሥራ ዕድል መስፋፋት የጀርባ አጥንት ነው።

አስተማማኝ እና ያልተቆራረጠ የኃይል አቅርቦት የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ቁልፍ ግብዓት ነው።

በመሆኑም ታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ምርት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የምርት ሥርዓት መሠረት መሆኑን መረዳት ይገባል።

ይህ ግዙፍ አቅም ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ከኃይል አቅርቦት ጋር በማስተሳሰር ከፍተኛ እሴት ለመፍጠር ያስችላላል።

በተለይም የማዕድን ሀብትን በጥሬው ከመላክ ይልቅ በሀገር ውስጥ በማቀነባበር፣ እንዲሁም የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በከፍተኛ ጥራት ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ኃይል በማሟላት የኢኮኖሚ አቅጣጫውን ይቀይረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በየደረጃው እየተገነቡ ያሉ የኃይል ማመንጫዎች የዚህ ትልቅ ራዕይ ማሳያዎች ናቸው።

በዚህ የምጣኔ ሀብት ጉዞ ውስጥ የብሪክስ (BRICS) አባልነት እና ትብብር ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል።

የብሪክስ አባል ሀገራት ያላቸውን የፋይናንስ አቅም፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንዱስትሪ ልምድ እና የማምረቻ ክህሎት ከኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል እና የሰው ሀብት ጋር ማጣመር የሚቻልበት ሰፊ መስክ ተከፍቷል።

ይህ ትብብር በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይወሰን፤ በኃይል ማከማቻ፣ በስርጭት መሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ማሽነሪ አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በዘመናዊ የሰው ኃይል ልማት ላይ ሰፊ ዐሻራ ያሳርፋል።

የታዳሽ ኃይል ልማት እና የብሪክስ ትብብር በተግባር ሲጣመሩ የማዕድን እና የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ይስፋፋሉ፤ የማምረቻ ዘርፉ ይነቃቃል፤ የወጣቶች የሥራ ዕድል ይጨምራል፤ እንዲሁም የኤክስፖርት ገቢ በእጅጉ ያድጋል።

በዚህም የተፈጥሮ ሀብት ወደ ምርት፣ ምርት ወደ እሴት፣ እሴት ወደ ሥራ እና የውጭ ምንዛሪ የሚቀየርበት ጠንካራ የኢኮኖሚ ሰንሰለት ይገነባል።

ታዳሽ ኃይል ለኢትዮጵያ የብርሃን ምንጭ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ ሽግግር እና የእሴት ፈጠራ የጀርባ አጥንት ነው።

ዓለም አቀፍ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ከሀገራችን የተፈጥሮ ጸጋ እና ታታሪ የሰው ኃይል ጋር ሲዋሃድ ኢትዮጵያ ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወደ አምራችነት እና እሴት ፈጣሪነት የምትሸጋገርበት አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ እውን ይሆናል።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: