Search

“የሚጨሰው ጠረጴዛ” የተሰኘው የጥበብ ሥራ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ለዕይታ ቀረበ

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 59

አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የተሰበሰቡበትን ታሪካዊ ክስተት በኪነ-ጥበብ የሚያወሳው እና የሚጨሰው ጠረጴዛ (The Smoking Table) የተሰኘው ድንቅ የጥበብ ሥራ፣ በዛሬው ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ለዕይታ ቀርቧል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው የአርት ፕሮፌሰር በሆኑት በፕሮፌሰር በቀለ መኮንን የተሠራው ይህ የጥበብ ሥራ፣ በኢትዮጵያ ለዕይታ ሲቀርብ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በጣሊያን ቀርቦ በበርካታ ዓለም አቀፍ ታዳሚዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል።

በኤግዚቢሽኑ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮሴፍ ቤኮ እና የሩሲያ፣ የቻይና እንዲሁም የሌሎች ወዳጅ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዮሴፍ ቤኮ፣ የተሰበሰብነው ያለፈውን ታሪክ ብቻ ልናወራ ሳይሆን፣ ያንን መሠረት አድርገን ወደፊታችንን በጽናት ልናንጽ ነው ሲሉ የዝግጅቱን ፋይዳ አስረድተዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ለዝግጅቱ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አጋር አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፣ ለፕሮፌሰር በቀለ መኮንን የላቀ የጥበብ አስተዋፅኦ ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፣ የአፍሪካን የመከፋፈል ታሪክ የሚወክለው ይህ ሥራ አፍሪካውያን በድል በደመቁበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ መቅረቡ ልዩ የታሪክ እና የሞራል ስሜት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን፣ ታሪካዊውን የመስከረም ዘጠኙን የክተት አዋጅ አስመልክቶ የመጀመሪያው የምክክር ጉባኤ ተካሂዷል።

ይህ የውይይት መድረክም በቀጣይ በየወሩ ተከታታይነት ባለው መልኩ እንደሚዘጋጅ አዘጋጆቹ ለኢቲቪ መዝናኛ አስታውቀዋል።

በሚሊዮን አደም

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: