Search

የመደመር ፍሬዎች፦ ከትውልድ ግንባታ እስከ ታላላቅ የልማት ስኬቶች

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 62

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ በርካታ የፈተና ማዕበሎችን ተሻግራለች። ከተጋረጡባት ውስብስብ ፈተናዎች ይልቅ ተስፋን ሰንቆ ሀገርን ወደ ከፍታ የሚያሸጋግር የታላቅነት ዕይታ ሁልጊዜም ያሸንፋል።

የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን ከተሰበረ ተስፋ እና ከተበታተነ አስተሳሰብ በማውጣት፣ ወደ ፈጣን የልማት ግስጋሴ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የታደሰ ብሔራዊ ኩራት ያሸጋገረ የዘመናችን ታላቅ ንቅናቄ ነው።

ይህ እሳቤ ከትውልድ አእምሮ ማነፅ ጀምሮ በዓይናችን እስከምናያቸው ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ድረስ የተመዘገቡ ታሪካዊ ስኬቶች መሠረት ሆኗል።

የማንኛውም ታላቅ ሀገር እውነተኛ መሠረት የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን የነቃ፣ በአዎንታዊ አስተሳሰብ የተቃኘ እና ለሀገሩ የሚቆረቁር ትውልድ መፍጠር ነው።

የመደመር እሳቤ ማኅበረሰብን በሚያንፁ እሴቶች ላይ በማተኮር "እኔ" ከሚለው ጠባብ ስሜት ይልቅ "እኛ" የሚል ማዕከላዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት አድርጓል።

ይህንን "እኛ" መንፈስ በተግባር ከሚያሳዩት ታላላቅ ክንውኖች መካከል፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 4 ሺህ ተወካዮችን ያሳተፈውን ዋና ሀገራዊ ጉባኤ በስኬት በማጠናቀቅ ጠቃሚ ምክረ ሀሳቦችን መሰብሰብ መቻሉ ቀዳሚው ነው።

ይህም የተበታተነ አመለካከት የነበረውን የማኅበረሰብ ክፍል በማቀራረብ ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ድል ነው።

የትውልድ ግንባታው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ብቻ ሳይወሰን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርም አድጓል።

5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ሥልጠና እንዲሁም የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ዘመኑን የሚዋጅ፣ ሀገሩን በዕውቀቱ እና በፍቅሩ የሚገነባ በራስ የመተማመን መንፈስ ያለው አዲስ ትውልድ እየቀረፁ ይገኛሉ።

የመደመር እሳቤ ከአስተሳሰብ አልፎ በተግባር ሲተረጎም፣ የኢትዮጵያን የመልክዓ ምድር ገጽታ ሙሉ በሙሉ የቀየሩ እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አዲስ የታላቅነት ማረጋገጫ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳችን አቅምና ብርታት በጨለማ ውስጥ ለነበሩ ሚሊዮኖች ብርሃን ማብሰር እንደምንችል ያረጋገጥንበት የብሔራዊ ኩራታችን ሕያው ተአምር ነው።

በተጨማሪም ከወንጪ እስከ ኮይሻ፣ ከጎርጎራ እስከ እንጦጦ እና ሀላላ ኬላ ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን በማልማት ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመረጠች የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ ተችሏል።

መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ዘመናዊ ያደረጉ ኮሪደር ልማቶች እንዲሁም የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማትን የመሳሰሉ ዐበይት ሥራዎች በፍጥነት ተከናውነዋል።

በግብርናው ዘርፍም የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት እና የበጋ ስንዴን በማልማት ኢትዮጵያን ከዘመናት የምግብ እህል ጥበቃ ወደ ኤክስፖርት አድራጊነት ያሸጋገረ ታሪካዊ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ተመዝግቧል።

ዛሬ ኢትዮጵያ በአሮጌ ችግሮች እና የታሪክ ገጾች ውስጥ ብቻ ተወስታ የምትቀር ሀገር አይደለችም። በመደመር እሳቤ መሪነት እያንዳንዱ የተተከለ ችግኝ፣ እያንዳንዱ የተገነባ የመሠረተ ልማት አውታር፣ በስኬት የተጠናቀቁ የውይይት መድረኮች እና በጠንካራ እሴት የተገነባው ትውልድ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ከፍታ እየመሯት ይገኛሉ።

ይህ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የነገዋን የበለጸገች፣ የተከበረች እና ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ የማይገታ የብልጽግና ጉዞ ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: