Search

ሀሳብ አልባ ፖለቲካ የፈጠረውን ታሪካዊ አዙሪት የሰበረው የመደመር ጉዞ

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 56

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) 'መደመር መንግሥት' መጽሐፋቸው "የሐሳብ አልባ ፖለቲካ ግብ ከሕግ በላይ ሆኖ ሀብት እና ሥልጣን መቀራመት ነው" ሲሉ ያስቀመጡት እሳቤ የዘመናዊ ታሪካችንን ፖለቲካ-ስብራት በጥልቀት የሚፈትሽ እውነት ነው።

በመደመር ብያኔ መሠረት ሐሳብ አልባ ፖለቲካ ማለት የፖለቲካ ሥልጣንን ከሕዝብ አገልግሎት እና ከተቋማዊ አሠራር በመነጠል፣ ለግል ጥቅም ማክበሪያነት የማዋል ፍጹም አፍራሽ አካሄድ ነው።

የፖለቲካ ተዋንያን የሐሳብ ልዕልናን ሲያጡ ሥልጣን የሕግ ማስከበሪያ መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ ከሕግ በላይ ይሆናል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ በዘመናዊው የፖለቲካ ታሪካችን ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዳያድጉ በማድረግ የሕዝብን ሀገራዊ ተስፋ ሲያጨልም ቆይቷል።

ይህ አካሄድያስከፈለን  ዋጋ እጅግ ከባድ ነው። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የነበሩ የሥልጣን ሽግግሮች አዲስ የመጣው ሁሉ የቀደመውን በጎ ነገር አፍርሶ ከዜሮ የመጀመር አክሳሪ አዙሪት ውስጥ የታሰሩ ነበሩ።

ከዘውዳዊው ሥርዓት እስከ ደርግ፣ ከዚያም እስከ ኢሕአዴግ የነበረው ጉዞ አንዱ ጥሎ ሌላው የሚነሳበት በመሆኑ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሳይገነቡ ቀርተዋል።

በዚህም ምክንያት ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከእኛ ኋላ የነበሩ ሀገራት ጭምር በጠንካራ ተቋማዊ መሠረት ተስፈንጥረው የዓለም የኢኮኖሚ ቁንጮ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ግን በእንደገና ጅምሮች እና በአለመረጋጋት ውስጥ እንድትባዝን ተደርጋለች።

2010 . ወዲህ ግን የመደመር መንግሥት ይህንን አክሳሪ አዙሪት በጽናት ለመስበር ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዷል።

መደመር አፍርሶ የመጀመርን አጥፊ ልማድ በመግታት፣ የትናንት አዎንታዊ ወረቶችን ጠብቆ ማስፋት እና የተሠሩ ስህተቶችን ማረም የሚያስችል ሀገር በቀል ፍልስፍናን በተግባር እያሳየ ነው።

ሥልጣን ለሕግ እና ለሥርዓት የበላይነት እንዲገዛ የማድረግ ተቋማዊ ማሻሻያዎች በፍትሕ፣ በጸጥታ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ተተግብረዋል።

የጽንፍ ፖለቲካን ለመታገልም እንደ ሽምግልና ያሉ ሀገር በቀል ጥበቦችን ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር በማጣመር አካታች የመግባባት ዴሞክራሲን መሠረት የሚያስይዝ ባህል እየተገነባ ይገኛል።

አሁን በተጀመረው የመደመር አካሄድ መፃኢው የኢትዮጵያ ተስፋ እጅግ ብሩህ ነው። አሁን ላይ የምናያቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት፣ የተጀመሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና የዲፕሎማሲ ድሎች የዚህ የሐሳብ ልዕልና ውጤቶች ናቸው።

ሐሳብ አልባነትን በሐሳብ ልዕልና፣ መከፋፈልን በመደመር፣ እንዲሁም አፍርሶ መገንባትን በይዞ ማደግ በመተካት የተጀመረው ይህ ጉዞ የነገዋን ኢትዮጵያ በጠንካራ ተቋማት መሰረት ላይ አቁሞ ለአፍሪካም አርአያ ወደምትሆንበት ማማ የሚያሸጋግር ዘላቂ መሠረት ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: