Search

ቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ ከኦስትሪያው ሊዮበን ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለውን የአካዳሚክ ትብብር አጠናከረ

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 63

በቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አብዲፈታህ አሕመድ ራቢ የሚመራው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ልዑክ፣ በኦስትሪያ በስቲሪያ ክልል ከሚገኘው የሊዮበን ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ (Montanuniversität Leoben) አመራሮች ጋር ስትራቴጂያዊ ውይይት አካሂዷል።

የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረገው ይኸው ልዑክ፣ በዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ቶማስ ፕሮሃስካ ከተመራው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ገንቢ እና ውጤታማ ምክክር ማድረጉ ተገልጿል።

ውይይቱ፣ ቀደም ሲል በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተጨባጭ የትምህርት ፕሮግራሞች በመቀየር ላይ ያተኮረ ነው።

የቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ 14 የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በፔትሮሊየም ምሕንድስና፣ በኢነርጂ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የላቀ ትምህርት እንዲከታተሉ ወደ ሊዮበን ዩኒቨርሲቲ እንደሚልክ ታውቋል፤ ይህም የትብብሩ የመጀመሪያ ፍሬ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ይህ እርምጃ የኢትዮጵያ የነዳጅ እና ጋዝ ምርት ብሔራዊ ፕሮግራም አካል ሲሆን፣ ቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ብሔራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለው መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የአካዳሚክ ትብብር የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲን በፔትሮሊየም ምሕንድስና ያለውን አቅም ከማሳደጉም ባሻገር፣ ለሀገራችን የኢነርጂ ዘርፍ ልማት ግቦች ስኬት እንዲሁም በሁለቱ ተቋማት መካከል ለሚኖረው ዘላቂ የሳይንስ እና የትምህርት ትሥሥር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀብሪደሀር ዩኒቨርሲቲ ሥር የተቋቋመው የነዳጅ እና ፔትሮሊየም ኢኒስቲትዩት ዘንድሮ 22 ልዩ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑ ይታወቃል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: