Search

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠውን ህልውናዋ ተጠብቆ የመኖር መብቷን ለማስከበር ወደ ቀይ ባሕር ትመለሳለች

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 119

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር፣ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር የተሣሠረ እና "ሕልውናዋ ተጠብቆ የመኖር መብት" (The Right to Exist) ማዕከል ያደረገ መሆኑን ተንታኞች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ እያነሣችው ያለው ጥያቄ፣ ከባሕር መዳረሻ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ ሉዓላዊት ሀገር በዓለም አቀፍ የንግድ እና የኢኮኖሚ ውህደት ውስጥ እኩል ተሳታፊ ሆኖ የመኖር መብቷን መሠረት ያደረገም ጭምር መሆኑን ያነሣሉ።

ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መሠረቶች መካከል በተባበሩት መንግሥታት የቻርተር ድንጋጌዎች ላይ "ማንኛውም ሀገር ሕልውናው ተጠብቆ የመኖር መብት አለው" በሚል ከተቀመጠው ዓለም አቀፍ መብት ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ የዚህን መሠረታዊ መብት አፈጻጸም በእጅጉ የገደበው ሲሆን፣ የባሕር በር ፍላጎቷም ይህንን መብት ለማስከበር የተወሰደ ስልታዊ እርምጃ ተደርጎ መታየት አለበት።

ማንኛውም ሀገር በራሱ አቅም የመኖር መብት አለው፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ በምጣኔ ሀብት እና በንግድ መስመሮች ላይ ነጻ መዳረሻ ሊኖረው ይገባል።

ኢትዮጵያም እየጠየቀች ያለችው ይህንን የተረጋገጠ መብቷን ነው። ከባሕር በር መገፋት፣ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ እንድትታፈን የሚያደርግ እና ዓለም አቀፍ ሕጎች ከሚደነግጉት የመኖር መብት ጋር የሚጋጭ ነው።

ሀገራችን በቀጣናው እያደረገች ያለችው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ፣ ግጭትን ሳይሆን "መረዳዳትን" (Understanding) መሠረት ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ጥያቄ ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ ነው፤ ስለዚህም የጎረቤት ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ፣ የሀገራችን የሕልውና ትግል አካል አድርገው መመልከት አለባቸው።

የመኖር መብትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለመገንባት ቁልፍ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ፣ እንደ ሀገር በዓለም መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ከማሳደጉም በላይ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተረጋገጠውን የመኖር መብቷን በተግባር እንድትጠቀም ያስችላታል።

በሰለሞን ከበደ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: