አተካና የሀዲያ ብሔር መገለጫ ከሆኑ ባህላዊ ምግቦች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በያሆዴ በዓል ከሚዘጋጁ ባህላዊ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
ምግቡ በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ ከአሠራሩ ጀምሮ እስከሚቀርብበት ዕቃ ድረስ የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው።
በያሆዴ በዓል አተካና ሲዘጋጅ ከዚህ ቀደም ለአተካና መስሪያነት ያገለገሉ ቁሳቁሶች በሙሉ በአዲስ ይተካሉ።
ለአተካና ማዘጋጃ የሚሆነው ቡላ ከእንሰት የሚመረት ሲሆን ለቡላ ምርት የሚሆኑ የእንሰት ዓይነቶችም ድሾ፣ ግሽራ፣ ጦሮራ፣ ቤኔጃ፣ ሀንዘና፣ አዎነዳ፣ ማርዕያ፣ ግንቦኦ፣ ግንጆና፣ ሞቼኤ፣ መርዛና እና የመሳሰሉት ናቸው።
አተካና በጉድጓድ ውስጥ እስከ አንድ ዓመት ከቆየ ቆጮ (Mereeero'o) የሚዘጋጅ ሲሆን የእንሰቱ ውስጠኛ ክፍል ተፍቆ በመፋቂያ እንጨት ስር በሚቀረው ቆጮ (ሜት/ሉጉዕሞ ዋሳ ጠፋ) ላይ ከቡላ ጋር የሚመሳሰል ነጭ ቆጮ፣ የተናጠ ወተትና የበሰለ ቅቤ ተጨምሮበት ይዘጋጃል።
ከተጠቀሱት የእንሰት ዓይነቶች የውስጠኛው ክፍል ተፍቆ የሚገኝ ነጭ ቡላ፣ አይብና በልኩ የበሰለ ቅቤ ይዘጋጃል።
አዲስ የተዘጋጁ ቡላ እና ቆጮ ለአተካና መስሪያነት ስለማይሆኑ የቆዩ መሆን አለባቸው።
በአተካና አዘገጃጀት ላይ እንደ ግምኤንጃ (በሶብላ)፣ ህጣና (ጠጅ ሳር)፣ እሽና ዳዳንች (ጦሲኝ)፣ ነጭ አዝሙድ (ቀዳል ኤንጃ)፣ ጥቁር አዝሙድ (ሄመች ኤንጃ)፣ ኮሮሪማ (ወግሽ)፣ አብሽ (ሽቆታ)፣ ዝንጅብል (ጀንጅቤል) እና ቀይ ሽንኩርት (ቢሻ) ያሉ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ይጨመራሉ።
በሀዲያ ብሔር ዘንድ ለአተካና የሚሆን ወተት በሶቢላ የተሰኘ ቅመም ተጨምሮበት፣ "ዋቶ" ተብሎ በሚታወቀው እንጨትና ሌሎች መልካም መዓዛ ባላቸው ዕጽዋት ጭስ በታጠነ እንስራ ውስጥ ከአስር ቀናት በፊት ጀምሮ ይጠራቀማል።
ምናልባት በመንደሩ ወተት የሌለው ቤተሰብ ካለ፣ ለአንድ ዙር የሚናጥ የእርጎ ወተት በእንስራ ይሰጠዋል።
ተቀባይዋም ቤተሰቡን በመመረቅ ወተቱን ንጣ አሬራውንና ቅቤውን ለይታ ትወስዳለች። በዚህ መልኩ የመንደሩ ሙሉ ቤተሰብ በበቂ ወተት የበዓሉን ምግብ እኩል ያዘጋጃል።
አተካና በያሆዴ በዓል ዋዜማ (በቅድመ ያሆዴ) ከሚበሉ የምግብ ዓይነቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ "የአተካና ምሽት" ተብሎ በሚጠራው በዚህ ምሽት የሚበላ ተወዳጅና ተናፋቂ ባህላዊ ምግብ ነው።
በዚህ ምሽት የያሆዴ አዲስ ዓመት መድረሱን እያበሰሩ በየቤቱ በ"ፉሊት ሂሞ" ለሚጨፍሩ ወጣቶች አተካና ይሰጣቸዋል።
ወጣቶቹ ከተመገቡ በኋላ አተካናውን የሰራችውን እናት በጭፈራቸውና በግጥማቸው ሙያዋን እያደነቁ ያሞግሷታል። አተካናው ጣዕም የሌለው ከሆነ ደግሞ እንዲሁ እየጨፈሩ ከሙያዋ ጋር አያይዘው በግጥም ሸንቆጥ ያደርጓታል።
ለዚህ ነው በሀዲያ ብሔር ባህላዊ የምግብ አሠራር ሥርዓት አተካና የሴቶች ልዩ ሙያዊ ችሎታ መፈተኛ ነው የሚባለው።
በሀዲያ ባህል መሠረት አተካና ለብቻ አይበላም። አተካና ተሠርቶ ሲያበቃ በዕድሜ የሚያንሱት ታናናሾች ወደሚበልጧቸው ታላላቆች ቤት ከነልጆቻቸው የተዘጋጀውን አተካና ይዘው በመሄድ ተመራርቀው ይመገባሉ።
አተካና ለአባወራ የሚቀርበው ከሸክላ በተሰራ "ቢጥራ" (ሻቴኤ) ሲሆን፣ ለልጆች ደግሞ ለእነርሱ ተብሎ በተዘጋጀ አነስ ባለ ቢጥራ ወይም በእሳት ተለብልቦ ለስለስ በተደረገ የኮባ (የእንሰት) ቅጠል ይሰጣቸዋል።
አተካና ሲቀርብ ዳጣ ወይም ናቀሮ እንደ ማባያ አብሮ ይቀርባል። ከአተካና ጎን ለጎን ከገብስ የተዘጋጀ ቦርዴ ወይም ቃሪቦ አሊያም ከማር የተዘጋጀ ብርዝ የመሳሰሉ ባህላዊ መጠጦች ይቀርባሉ።
አተካና ለሰውነት የማይከብድና የምግብ ፍላጎትን የሚጨምር እንዲሁም ለበርካታ የጤና ችግሮች መድኃኒትነት ያለው ምግብ እንደሆነ ይነገራል።
በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ አተካና በማኅበረሰቡ ባህላዊ ጥበብና ዕውቀት መሠረት በአግባቡ ሲቀመጥ ሳይበላሽ እስከ 6 ወር ይቆያል።
በሰብለወርቅ ኤልያስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: