በተከታታይ ለ8 ዓመታት የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በመሆን አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደፊትም ምርጥነቱን ለማስቀጠል በከፍተኛ ወጪ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አቡሴራ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ በ3975 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው፡፡
የአውሮፕላኑ ማረፊያው በ2 ምእራፍ የሚገነባ ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የሚሰራ ነው፡፡ 2ኛው ምዕራፍ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ያስችላል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው ዘመናዊ ሁለት ተርሚናሎች፣ሁለት የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች፣የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ማስተናገጃ ማዕከል፣ የበረራ የመቆጣጠሪያ፣ የመንገደኞች ማስተናገጃዎች፣ ዘመናዊ ሆቴሎችና መዝናኛዎች፣ የንግድ ማእከላትን ጨምሮ ሌሎች በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ማእከላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው “የአውሮፕላን ማረፊያ እጅግ ዘመናዊ ሆኖ በዓለም ከምናያቸው ጥቂት ቦታዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ነው የገለፁት፡፡
ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 20 በመቶ በአየር መንገዱ የሚሸፈን ሲሆን 80 በመቶ የአፍሪካ ልማት ባንክና በሌሎች ባንኮች ፋይናንስ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ 500 ሚሊዮን የአሜሪከ ዶላር ብድር ለመስጠት ከስምምነት ላይ የደረሰው የአፍሪካ ልማት ባንክ የፊታችን መስከረም ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ይዟል፡፡
በአፍሪካ ትልቁ የቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል የአውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌ ኢንተርናሽናል የአውሮፕላን ማረፊያ በፈጣን ባቡር እንዲገናኝ ይደረጋል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው መገንባት በኢትዮጵያ በኩል ለሚያልፉ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ ግዙፉን የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ብዙ እርምጃ ወደፊት ሄደናል ያሉት አቶ መስፍን የአውሮፕላን ማረፊያው ዲዛይን እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
"የግንባታ ቦታውን ካርታ ተረክበናል፤ ከይዞታቸው ለሚነሱ 2500 አርሶ አደሮች ተለዋጭ መኖሪያ ቤት እና የንግድ መስሪያ ህንፃ እየተገነባ ነው። ግንባታውም እስከ መስከረም ተጠናቆ በህዳር ወር ውስጥ የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ይጀመራል" ብለዋል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ብለዋል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢን የማይበክል ቴክኖሎጂን፣ የፀሐይ ኃይል የሚጠቀም፣ ዘላቂነት ያለው የቆሻሻ ማስወገጃና የውሃ አጠቃቀም ስርዓት እንዲኖረው በሚያስችል ዲዛይን የተሰራ በመሆኑ በአካባቢ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አያስከትልም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ በከፍተኛ ወጪ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካውያንን ትስስር በማጠናከር የአፍሪካ ህብረት "የተዋሀደችና የተሳሰረች አፍሪካን እውን ማድረግ" በሚል የያዘው ራዕይ እንዲሳካ ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡
በላሉ ኢታላ