Search

ከ3 አስርት ዓመታት በኋላም መጠናቀቅ ባለመቻሉ ወደ ግዙፍ የቪዲዮ ስክሪንነት የተቀየረው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 4478

በሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ ግንባታው በተጀመረበት ዓመታት ከዓለማችን አስር ግዙፍ ህንጻዎች መካከል ተመድቦ የነበረ ትልቅና በመስታወት የተለበጠ ባለሦስት ማዕዘን ሕንጻ ከርቀት ቆሞ ይታያል።

ይህ በመሐል ከተማዋ  የሚገኘውና በተለይ በምሽት ለከተማዋ ትልቅ ድምቀት የሚሰጠው አስገራሚ ዲዛይን ያለው ግዙፍ ሕንጻ፤ በላዩ ላይ በተገጠሙት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኤል መብራቶች አማካኝነት የተለያዩ ሙዚቃዎችን  የርችት ምስሎችንና የሀገሪቱ ቴሌቪዥን መልእዕክቶችን በግዙፍ ስክሪኑ ያሳያል።

ርግዮንግ ሆቴል በመባል የሚታወቀው ይህ የርግያንግ ባለ 105 ፎቅ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ለመገንባት ዓመታትን የወሰደ ሲሆን 1.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ፈጅቷል።

ከውጭ ሲታይ የሚያስገርመው ሕንጻ በውስጡ 3 ሺህ ያህል የሆቴል ክፍሎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራ ሲሆን በዓይነታቸው ለየት ያሉና የፒዮንግያንግ ከተማን ከያቅጣጫው የሚያሳዩ አምስት ተሽከርካሪ ሬስቶራንቶችንም አካትቶ የያዘ ነበር

የሆቴሉ ግንባታ የተጀመረው 1987 ሲሆን ስራው ለረጅም ጊዜያት ሲጓተት ከቆየ በኋላ፣ የሶቪየት ህብረትን መውደቅ ተከትሎ በተዳከመው የሰሜን ኮሪያ ኤኮኖሚ ምክንያት በኋላም በተለያዩ ማዕቀቦች በተፈጠረው የኤኮኖሚ ቀውስ 1992 ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ባለበት እንዲቆም ተደረገ

በዚህ መልኩ ዓመታት ከቆየ በኋላ በአንድ የግብፅ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ አማካኝነት የህንጻው የውጭ ክፍል በመስታወት እንዲሸፈን ተደርጎ የተሻለ ገፅታ ተላበሰ።

ሆኖም በተለይ የውስጠኛው ክፍል ባለማለቁ ምክንያት አገልግሎት ሊሰጥ ስላልቻለ፣ የህንጻው ውስጠኛ ክፍል እየተጎዳ በተለይ እንደመወጣጫ ሊፍት ያሉ ብዙ ብር የወጣባቸው እቃዎች ከጥቅም ውጭ መሆን ጀምረዋል።

የሰሜን ኮሪያ መንግስት ከአንድ ቢሊየን ብር ወጭ ወጥቶበት ሊጠናቀቅ ያልቻለውን ይህን ግዙፍ ህንጻ በተመለከተ 2012 ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ሲል ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፤ እስከ አሁን እውን ሳይሆን ዓመታትን አስቆጥሯል።

እንደውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  ይህ 3 ሺህ ክፍሎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራው ሆቴል ወደ ትልቅ ስክሪንነት ተለውጧል

ታላቁ የርግያንግ ሆቴል ላይ 1 መቶ ሺህ በላይ የኤል መብራቶችን በመግጠም የተለያዩ ዲጂታል መልእክቶች ይተላለፉበታል

ከጥቂት ጊዜያት በፊት አንድ የጀርመን የሆቴል ድርጅት ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት አስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ሳይጠናቀቅ ዓመታት የፈጀውን ሆቴል ጨርሶ ወደ ሆቴልነት ለመለወጥ እስካሁን ከወጣበት ወጪ ሌላ 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚፈጅ በመታወቁ ሀሳቡን ሰርዟል።

ከውጭ ሲታይ አስገራሚ ዲዛይን ያለው ይህ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የፈጀ የሰሜን ኮሪያ ያላለቀ ሆቴል ውስጡ ባዶ ሆኖ ግዙፍ የቪዲዮ ስክሪን ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

በዋሲሁን ተስፋዬ