Search

"መረጃን ከማጋራት በፊት በሀገራዊ ኃላፊነት ስሜት አጣርቶ መጠቀም አስፈላጊ ነው"

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 100

መረጃን ከማጋራት በፊት በሀገራዊ ፍቅር እና በኃላፊነት ስሜት አጣርቶ መጠቀም አስፈላጊ ነው ሲሉ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የህዝብ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ግርማው አሸብር ገልፀዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ያነሱት ግርማው፤ በተለይ የጥላቻ እና ሐሰተኛ መረጃዎች የሚያስከትሉት ተፅዕኖ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የጥላቻ እና ሐሰተኛ መረጃዎች መገለጫዎችም የማህበረሰብ ክፍፍል፣ የግጭት መጨመር፣ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር፣ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን መፍጠር፣ ዓመፅ እና ግጭትን ማባባስ ብሎም የፕረስ ነፃነትን መጋፋት ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።
በተለይ ሐሰተኛ መረጃዎች በህብረተሰቡ ዘንድ የተዛባ ትርክት እና አመለካከት ፈጥረው መተማመን እና መግባባት እንዲቀንስ በማድረግ ጫና እንደሚያሳድሩ ነው አቶ ግርማው የገለፁት።
እነዚህን ተፅዕኖዎች ለመከላከልም ማህበረሰቡ በተቻለ መጠን እምነት ከሚጣልባቸው ገፆች ብቻ መረጃዎችን እንዲወስድ እና የተጋሩ መረጃዎች ለምን ዓላማ እንደተለጠፉ ማገናዘብ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገር የሃሰተኛ እና የጥላቻ መረጃዎችን ተፅዕኖ የሚያሳዩ ግንዛቤ መስጫ መድረኮችን ማዘጋጀት እና በእነዚህ መረጃዎች የተጎዱ ሰዎችን ታሪክ በዶክመንተሪ መልክ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ስለ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከስር ጀምሮ ታዳጊዎችን ማስተማር፣ ሐሰተኛ መረጃዎች የሚገቱበት ስትራቴጂዎችን መንደፍ ፣ መረጃዎችን የሚያጣሩ "ፋክት ቼክ" የሚያጋሩ ገፆችን ማበረታታት ደግሞ ሌላው አማራጭ ነው ብለዋል።
በሴራን ታደሰ