Search

በውጭ ሀገራት ለሥራ ለሚሰማሩ ዜጎች የሚያገለግለው “ለመንገዴ” የተሰኘው መተግበሪያ

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 165

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በመተባባር በውጭ ሀገራት ሥራ ለሚሰማሩ ዜጎች የሚያገለግል “ለመንገዴ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያን ይፋ አድርጓል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ነቢሃ ሙሐመድ የሞባይል መተግበሪያው ዜጎች ለሥራ ስለሚሄዱበት ሃገር በቂ መረጃ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዜጎች በመዳረሻ ሀገራት በሚኖራቸው ቆይታ ችግር ቢገጥማቸው ሪፖርት ለማድረግ እንደሚያስችላቸው እና መብት እና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

መተግበሪያው ዜጎች በውጪ ሀገራት የሥራ ስምሪት በሕጋዊ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የዓለም የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በበኩላቸው፥ መተግበሪያው ዜጎች በተለያዩ ሀገራት የሥራ እድል እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ መብት እና ደህንነታቸውን እንዲገነዘቡ ይረዳል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው ለመንገዴ መተግበሪያ በቴሌብር ላይ የሚገኝ ሲሆን በአማርኛ፣ በአረብኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

 

በአሚር ጌቱ