Search

አደጋ ባለማድረስ የሚመሰገኑት - የአሶሳ ሴት የባጃጅ ሾፌሮች

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 180


አሶሳ ከተማ በተለምዶ ባጃጅ የሚባሉትን ባለሦስት እግር ተሽከርካዎች ላይ የሚሰሩ  በርካታ ሴት ሾፌሮች አሏት። 

እነዚህ ሴት ሾፌሮች ታዲያ የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በከተማዋ ተወዳጅነትን ማትረፋቸውን የትራፊክ ፖሊሶች ጭምር ይመሰክራሉ። 

 



በአሶሳ የባጃጅ ሾፌር የሆኑት በይዳ አዩብ እና አጫልቱ ምትኩ፤ ለረጅም ዓመታት ሲሰሩ አንድም ቀን አደጋ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ።

በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት የትራፊክ ሕግን አክብረው፤ በእርጋታ ማሽከርከርን ምርጫቸው ማድረጋቸውንም ነው የሚናገሩት።

 



በአሶሳ በተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋ እንደሚደርስ አስታውሰው፤ ይህም ከአሽከርካሪዎች ፍጥነት ጋር እንደሚያያዝ እና መፍትሄውም ሕግን አክብሮ በእርጋታ ማሽከርከር መሆኑን አንስተዋል።

በአሶሳ የወረዳ ሁለት  የትራፊክ ፓሊስ አስተባባሪ የሆኑት ኢንስፔክተር ጀማል ቃሲም በበኩላቸው፤ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

አደጋዎቹን በመቀነስ ረገድ ሴት የባጃጅ አሽከርካሪዎች የተሻሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤  ሙያዊ ስነ-ምግባር እና ተሞክሯቸው ለሌሎችም የሚተርፍ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በየጊዜው የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስም ሁሉም በጥንቃቄ በማሽከርከር ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በቢታኒያ ሲሳይ