Search

የተፋሰሱን ሀገራት ከጎርፍ አደጋ፤ የዓባይን ውኃ ከብክነት የሚታደገው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

ዓርብ ነሐሴ 16, 2017 2448

የአፍሪካ ትልቁ ስለሆነው የሕዳሴ ግድብ ከኃይል አመንጭነቱ ባሻገር ስላለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በአሜሪካ የሲቪል መሐንዲሶች ማህበረሰብ ድረ-ገፅ ሰፋ ያለ ትንታኔ ቀርቧል።

በድረ-ገፁ በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ የመሬት እና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል የውኃ ሀብት ምህንድስና ተመራማሪው አሰፋ መለሰ (/) እና በሂዩስተን የሚገኘው ኢንቴክ ሲቪል መሐንዲሶች ተቋም የውኃ ሀብት አጠቃቀም አስተባባሪው አለማየሁ ገብርኤል ሰፋ ያለ ጽሑፍ አስነብበዋል።

በጽሑፋቸውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተቀዳሚ ተግባሩ ከሆነው ኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አስቀምጠዋል።

ግድቡ ለጎርፍ መቆጣጠሪያ መለኪያ፣ የጥቁር ዓባይን ፍሰት ለመቆጣጠር እና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም በሱዳን ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን አውዳሚ የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ይረዳል ብለዋል ምሁራኑ።

የግድቡ ውኃ የመያዝ አቅም በመስኖ የግብርና ምርታማነትን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃልም ያሉ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን ሀገራት ጭምር የሚጠቅም መሆኑን ገልጸዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም ስንመለከተው ግድቡ ኢትዮጵያ ኃይልን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን እንድታሳድግ ትልቅ እድል የፈጥርላታልም ብለው፤ ይህም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ ተጨማሪ ማስፈንጠሪያ ሊሆን እንደሚችልም ነው ያነሱት።

ከምንም በላይ ደግሞ ከሀገራዊ እይታ አንጻር ግድቡ የኢትዮጵያውያን ኩራት እና በራስ የመተማመን ምልክት ሆኖ የቆመ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም አገሪቷ ራሷን ችላ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የማከናወን እና ፋይናንስ የማድረግ አቅም እንዳላት ያሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ታዳጊ ሀገራትን ጭምር የውጭ ዕርዳታ ላይ የተመረኮዙ የልማት ሥራዎችን ቀስ በቀስ በመላቀቅ በራስ አቅም ወደ ማልማት የሚያሸጋግር ድልድይ እንደሆነም ምሁራኑ በጽሑፋቸው አስነብበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሂደት የግድብ ጉዳይ ብቻ አይደለም የሚሉት ምሁራኑ፤ ግድቡ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ታሪካዊ የወንዞች ተፋሰሶች አንዱ በሆነው የዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ቀጣናዊ ትብብር፣ ዘላቂ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሚና የሚኖረው መሆኑን አስምረውበታል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ የውኃ ኃይል ማመንጫ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ ከሚያበረክተው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ በዓባይ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ ሃገራትን ከጎርፍ አደጋ የሚጠብቅ ብሎም የተፋሰሱን የውኃ ብክነት የሚቀንስ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

... 2011 ፕሮጀክቱ መገንባት ሲጀምር 30 በመቶ ያነሱ ኢትዮጵያውያን ብቻ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ነበሩ። ይህም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት እና የዜጎችን ሕይወት በእጅጉ የጎዳም ነው።

ግድቡ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ከእጥፍ በላይ እንደሚያሳድግ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያን የኃይል እጥረት ካለባት ሀገር ወደ ምስራቅ አፍሪካ ዋና የኃይል አቅራቢነት እንደሚያሸጋግራት ይጠበቃል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ግንባታ ብሎም ጂኦፖለቲካዊ ውዝግቦችን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ፤ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የዓባይ ወንዝን ለኃይል ማመንጫነት የመጠቀም ሀሳብ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሀሳብ ሆኖ የቆየም ነው። ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል የቴክኖሎጂም ሆነ  የገንዘብ አቅም ሀገሪቱ አልነበራትም።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘመናዊ ገጽ የተገለጠውም ለበርካታ አስርት ዓመታት የተደራጁትን በርካታ ጥናቶችና ውይይቶች ይዞ ነው።

በሰለሞን ከበደ