Search

'ስለ ባሕር በር አትጠይቁ' ከሚል 'የትውልድ ጥያቄ ነው' ወደሚል አቋም መሸጋገር ችለናል፡- ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ

ዓርብ ነሐሴ 16, 2017 116

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳልነበራት ለሚያስቡ አካላት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መልስ መስጠት የሚያስችለውን የሀገሩን ታሪክ በሚገባ ማወቅ አለበት ሲሉ ይገልጻሉ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ በቀጣናው የነበራትን ተሳትፎ እና ግዛት ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የነበራት የባሕር ኃይል የቀይ ባሕር እና ዙሪያውን ሰላም በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡

በወቅቱ የነበረው የባሕር ኃይል በብርቱ የተደራጀ እንደነበር አስታውሰው፤ መርከብ ለማስጠገን እና ለሌሎች  እንቅስቃሴዎች 'ዲያጎ ጋርሲያ' ወደብ ድረስ የሚያቀና ቡድን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

"ይህ ሁሉ ተረስቶ 'የባሕር በር ይገባናል በማለት አትጠይቁ' የሚባልበት ወቅት መጥቶ ነበር" ሲሉ ፕሮፌሰር ብሩክ

ይገልጻሉ፡፡

አያይዘውም 'ስለ ባሕር በር አትጠይቁ' ከሚል 'የትውልድ ጥያቄ ነው' ወደሚል አቋም መሸጋገር ችለናል፤ ይህም ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡

"ይህ በርካታ ሀገራት የደገፉት ጥያቄያችን ጊዜው ቢረዝምም፣ ምላሽ እንደሚያገኝ እርግጥ ነው" ሲሉም የታሪክ ምሁሩ አክለዋል፡፡

በርካታ ሀገራት ርቀት ሳይገድባቸው የጦር ሰፈር በመሰረቱበት ቀጠና፣ ኢትዮጵያ ሌላ አማራጭ አለማበጀቷ አስጊ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡

ፕሮፌሰር ብሩክ ከ95 በመቶ በላይ የገቢ እና ወጪ ንግድ ለማስተላለፍ የምንጠቀመው የጅቡቲ ኮሪደር በተገማች እና በሌላ መልኩ እክል ቢያጋጥመው፣ ህልውናችን ምን ይሆናል የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ 

የመንግስት እና የህዝብ የጋራ ጥያቄ የሆነው ይህንን ሃሳብም ከግብ በማድረስ መተንፈሻ ያላት ሀገር ለልጆቻችን እናወርሳለን ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

በአፎሚያ ክበበው