Search

የጋሞ ማኅበረሰብ የችግር አፈታት ባህል - ዱቡሻ

ዓርብ ነሐሴ 16, 2017 85


'ዱቡሻ' የጋሞ ማኅበረሰብ የችግር አፈታት ባህል ሲሆን የአካባቢው የፍትሕ ሥርዓት ነው።

የጋሞ ማኅበረሰብ የችግር አፈታት ሥርዓት የሆነው ዱቡሻ የተበደለ ሰው ፍርድ የሚያገኝበት አደባባይ እንደሆነ የሚናገሩት የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ አበበ አጡራ ናቸው።

ይህ ፍርድ የሚሰጥበት ቦታ ሰዎች ችግራቸውን በኃይል ከመፍታት ይልቅ፤ በሥርዓት በወግ እና ባህል ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የሚደረግበት የፍትሕ ተቋም ነው ሲሉም ይገልጹታል።

የሀገር ሽማግሌዎች ቦታ ቦታቸውን ይዘው ሳር በመበጠስ ድንጋይ ላይ በማስቀመጥ እሱ ላይ እንደሚቀመጡ የሀገር ሽማግሌ አበበ አጡራ ይገልጻሉ። የዚህም ተግባር ትርጓሜ ኑሮን ሁሉ እርጥብ ያድርግልን የሚል መልዕክት አለው።

በዱቡሻ አለመግባባትን ለመፍታት የሚሄዱ ሽማሌዎች፥ የመልካም ስብዕና እና የቀና ልቦና ምልክት የሆነው የጋሞ አባቶች አለባበስ ቀለመ ደማቁን ድንጉዛ ለብሰው እና የማኅበረሰቡ የክብር በትር የሆነውን ዳንባሮ ወይም ሆርሶ ይዘው እንደሆነም ይገልጻሉ።

በዳይም ሆነ ተበዳይ ለዱቡሻ ሲመጣ ጫንባራን ይዞ ቡሉኮ፣ ፓርዢያ ይዞ መምጣት ግዴታ መሆኑን የሀገር ሽማግሌው ይናገራሉ።

በእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ 4 አስታራቂ ሽማግሌዎች የሚቀመጡ ሲሆን፤ ሕዝብ ሆይ ታርቀህ ተነስ ሰላም ይስጥህ ብለውም ይቀመጣሉ።

ይህ የፍትህ ሥርዓት የራሱ ሕግና ደንብም እንዳለውም አክለዋል።

በሜሮን ንብረት