5ኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በውሎው በቀረቡለት 2 ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል።
ካቢኔው በቅድሚያ በመንግሥትና የግል አጋርነት ጽ/ቤት የተፈረመውን የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስምምነት ላይ ተወያይቷል።
ከ733 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቁ የተነገረላቸው 30 ፕሮጀክቶች፣ 37 አልሚዎችን የሚያሳትፉ መሆናቸው ተገልጿል።
ካቢኔው ፕሮጀክቶቹ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ የሚፈጥሩትን ሰፊ የሥራ ዕድል እና አዲሱ የአጋርነት አሠራር ያለውን ትልቅ ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ ስምምነቱን አጽድቋል።
ካቢኔው በመቀጠል የተወያየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የአሰልጣኞች የዝውውርና የምደባ አፈፃፀምን በተመለከተ በቀረበለት ረቂቅ ደንብ ላይ ነው።
ደንቡ በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ጥራት ያለው ሥልጠና ለመስጠት፣ ኮሌጆችን ውጤታማ ለማድረግ እና በተደራጀ አግባብ ለመምራት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሏል።
ካቢኔው በረቂቅ ደንቡ ላይ በጥልቀት በመወያየት ማጽደቁን የከንቲባ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የኦንላይን ሚዲያ አስተዳደር ዳይሬክተር ብሩክሰው ይልማ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
#ኢቢሲዶትስትሪም #አዲስአበባ #ኮሪደርልማት #ወንዝዳርቻልማት