የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ የፓኪስታን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ ለሚያከናውኑት ምርምርና ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ለምትሰጠው ተግባራዊ ምላሽ መሠረት የሚጥል መሆኑን የተቋማቱ ምሁራን ገለፁ።
በታዳጊ ሀገራት የአረንጓዴ ልማትን፣ ፈጠራን እና ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን በብቃት ለመዋጋት ያለመ የኢትዮ-ፓኪስታን የአረንጓዴ አሻራ ውይይት በላሆር ተካሂዷል።
በዚህም ወጣቶችን ይዞ ወደ በፓኪስታን ያቀናው የአረንጓዴ ዲያሎግ ዲፕሎማሲ ቡድን ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ የአየር ንብረት ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ፓኪስታናውያን ጋር ተወያይቷል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በመድረኩ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን አስከፊ ተፅዕኖ ለመግታት ህዝባዊ ንቅናቄ ፈጥሮ ሰፊ የችግኝ ተከላ በማከናወን የተገኘውን ውጤታማ ተሞክሮ አጋርተዋል።
ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል አመራር የተመዘገበ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት መሆኑን በማብራራት፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ያካበተችውን ልምድ ለፓኪስታን በማጋራት በአብሮነት ትሠራለች ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያውያን ባለፉት 7 ዓመታት ባደረጉት የጋራ ርብርብ ከ47 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የምግብ ዋስትና እጦትን፣ የዐፈር መሸርሸርን፣ ድህነትን እና ሥራ አጥነትን ለማቃለል መቻሉን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በምታደርገው እንቅስቃሴ ያገኘችውን የካበተ ልምድ ለፓኪስታን ለማጋራት የጀመረችው ጥረት ሀገሪቱ ችግሩን በዓለም አቀፍ አውድ ለመታገል ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
በፓኪስታን ላሆር በተካሄደው መድረክ የተሳተፉ የዩኒቨርስቲ ምሁራን የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ትልቅ ግብዓት የሚሆን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተሞክሮ ፓኪስታን የአየር ንብረት ለውጥን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የፑንጃብ ፓርኮችና ሆርቲካልቸር ባለስልጣን በበኩሉ፥ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በማድነቅ በዚህ ረገድ ከሀገሪቱ ጋር የመሰረተውን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።
በሁለቱ ሀገራት ተወካዮች መካከል የተካሄደው ውይይትም የፑንጃብ ግዛት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ ከዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎቹ ጋር አጣጥሞ እንዲሄድ የሚያስችለው መሆኑንም ገልጿል።
በላሆር ከተካሄደው ውይይት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ለአረንጓዴ ልማት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ የችግኝ ተከላ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሰዒድ ዓለሙ
#EBCdotstream #ETV #Ethiopia_Pkistan #GreenLegacy #GreenDiplomacy