የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትን በሚገባ በማስተዋወቅ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገቡ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ሲሉ የቱሪዝም ባለሙያ እና አማካሪው አሸናፊ ካሳ ገለፁ።
አቶ አሸናፊ ከኢቲቪ ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በዓላቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይበልጥ እየታወቁና የሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ እየሆኑ ስለመምጣታቸው አንስተው፤ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ መከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።
በዓላቱ ለሴቶች ነጻነት የሚሰጡ እና ወደ አደባባይ የሚያመጧቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሴቶች አምረው እና ተውበው ባህላቸውን የሚያስተዋውቁባቸው ስለመሆናቸው አክለዋል።
የውጭ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሊያዩዋቸው ከሚፈልጓቸው ነገሮች መካከል ባህል ዋነኛው ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ይህ የሚገኘው ደግሞ በመሰል ክብረ-በዓላት እና በገበያ ስፍራዎች ስለመሆኑ አንስተዋል።
በትግራይ እና አማራ ክልልሎች ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበሩትና የአዲስ ዓመት መዳረሻ የሆኑት በዓላቱ ከቱሪስት መስህብነት ጎን ለጎን በሥራ ዕድል ፈጠራም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ነው የገለፁት።
በሜሮን ንብረት
#ኢቢሲዶትስትሪም #አሸንዳ #አሸንድዬ #ሻደይ #ሶለል