ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በኤልዶሬት ኬንያ በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ለሀገራቸው ነጻነት ለታገሉና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ያላቸውን ታላቅ ክብር ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ለኬንያ ጀግኖች የጀግንነት ታሪክ እና ትተውት ላለፉት ዐሻራ የላቀ ክብር እንዳላቸው ገልጸው፤ የኬንያ የጀግንነት እና የመስዋዕትነት ታሪክ፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመከላከል በአንድነት ከቆሙበት ከኢትዮጵያ የአድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል አብራርተዋል።
እነዚህ የጋራ ታሪኮች ነጻነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በመስዋዕትነት የተረጋገጠ መሆኑን የሚያስገነዝቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አክለውም ታሪካችን የተሳሰረ እንደመሆኑ ሁሉ የወደፊት እጣ ፈንታችንም እንዲሁ የተሳሰረ ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በመደመር መንፈስ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለህዝቦቻቸው ሰፊ እድሎችን እና የጋራ ብልጽግናን ለመፍጠር በንጹህ ሀይል፣ በመንገድ ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በንግድ ዘርፎች ያላቸውን ነባር ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ክብር ለተቸራቸው ጀግኖች ሁሉ ላቅ ያለ አክብሮታቸውን በማቅረብ መልካም የማሹጃ (የጀግኖች) ቀን መልእክት አስተላልፈዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: