Search

የዘንድሮውን የሐጅ ምዝገባ ጥቅምት 12 ቀን ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቅቋል፡- የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

ማክሰኞ ጥቅምት 10, 2019 41

የ1448 ዓመተ ሂጅራ (2019 ዓ.ም) የሐጅ ጉዞ ምዝገባ የፊታችን ሐሙስ ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይፋ አደረገ።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ "የላቀ አገልግሎት ለሀጃጅ እርካታ" በሚል መሪ ቃል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሐጅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚጓዙ ምእመናንን በተሳለጠ መንገድ ለማስተናገድ 33 የምዝገባ ማስተባበሪያ ጣቢያዎችን ማዘጋጀቱን ገልጿል።

በወጣው መርሃ-ግብር መሠረት የምዝገባ ጊዜ ከጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 10 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል። የዘንድሮው የሐጅ አገልግሎት ክፍያ 827,000.00 (ስምንት መቶ ሃያ ሰባት ሺህ ብር) መሆኑ ተጠቅሷል።

የዘንድሮው ምዝገባ ቀደም ብሎ እንዲጀመር የተደረገው የሳዑዲ ዓረቢያ ሐጅ ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሠረት ሲሆን፤ ሂደቱን ቀድሞ ማካሄድ በኋላ ላይ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ እንግልቶችን ከመቀነሱም ባሻገር ለሀጃጆች የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ ሰፊ ፋይዳ እንደሚኖረው ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሀገራዊ ክብር የሚመጥን እና ቀልጣፋ አገልግሎት በሳዑዲ ዓረብያ ለዜጎች ለመስጠት በርካታ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

ባለፈው 1447 ዓ.ሂ የሐጅ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባሳየው የላቀ የቅንጅትና የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃት ከሳዑዲ ዓረቢያ ሐጅ ሚኒስቴር ከፍተኛ የክብር ማዕረግ የሆነውን "ለበይቱም የአልማዝ" (Diamond Award) ሽልማት ማግኘቱ ይታወሳል።

የሐጅ ሥነ-ሥርዓት በእስልምና እምነት ውስጥ ከተቀመጡት አምስት መሠረታዊ የእምነቱ ማዕዘናት አንዱ ሲሆን፤ የአካልና የገንዘብ አቅም ላለው ማንኛውም ሙስሊም በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ወደ ቅዱሳን ስፍራዎች በመጓዝ የሐጅ ጉዞ ማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው።

 

በመሐመድ ራህመቶ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: