Search

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች እየተካሄደ ነው

ረቡዕ ጥቅምት 11, 2019 40

በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ሀገር አፍራሽ የሆኑ የባንዳና የባዳዎችን የጥፋት እኩይ ሴራ የሚያወግዝ እና ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነት የሚያረጋግጥ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ከጠዋቱ ጀምሮ እየተካሄደ ነው።

ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ በቦረና መካነሰላም፣ በሀርቡ፣ በወረባቦ ወረዳ ቢስቲማ ከተማ፣ በቃሉ ወረዳ ደጋን ከተማ እና በወረኢሉ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በሰልፉ ላይ የተሳተፉ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊቱን ገድልና ሀገራዊ አለኝታነት የሚያወሱ እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ በርካታ መፈክሮችን አስተጋብተዋል።

በሕዝባዊ ሰልፉ ከተንጸባረቁት ዋና ዋና መልዕክቶች መካከል "ከውኃ እስከ ውኃ፣ ከታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ወደ ቀይ ባሕር ወደባችን የምናደርገውን ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስልታዊ ሽግግር በሁለንተናዊ አቅማችን፣ በጉልበታችን፣ በእውቀታችንና በሙሉ ልባችን በይፋ እንደግፋለን!" ይገኝበታል፡፡

"የጀግናውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ ማስከበር ዘመቻ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተከናወኑ ያሉ የጀግንነት ሥራዎችን እንደግፋለን!" ከተሰሙ መፍክሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በድጋፍ ሰልፉ የተሳተፉት ነዋሪዎች ሀገር የማፍረስ ሴራቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎችን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጸው፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስከበርና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ተጋድሎ እስከ መጨረሻው ከጎኑ በመቆም ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተስፋሁን ደስታው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: