የአፍሪካ ሀገራት አስተማማኝና ነፃ የመረጃና ስታቲስቲክስ ሥርዓት ለመዘርጋት በዘርፉ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው 10ኛው የአፍሪካ የስታቲስቲክስ ኮሚሽን ጉባዔ መክፈቻ ላይ እንዳሉት አፍሪካውያን የዳታ እና ስታቲስቲክስ ሥርዓታቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ጥረት ማሳደግ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በስታቲስቲክስና በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፍ ያስመዘገበቻቸውን ተሞክሮዎች ያነሱት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ የብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ መተግበሩ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት መደረጉ እና እርስ በእርስ የሚገናኙ ዘመናዊ የክፍያ መሠረተ ልማቶች መዘርጋታቸው አበረታች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ በስራ ላይ የዋለው የ"ፋይዳ" ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ፣ ኢትዮጵያ አገልግሎቶችን በቀላሉ፣ በቀልጣፋና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ለዜጎቿ ተደራሽ እንድታደርግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ጉባዔው በአባል ሀገራት እየተከናወኑ ያሉ ዓለም አቀፍ ፕሮግራሞች መነሻ ያደረጉ ስራዎችን ለመገምገም እና የስታቲስቲክስ አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው።
በተለይም የሕግና የተቋማት ማዕቀፎችን ማጠናከር፤ በሀገር አቀፍ የስታቲስቲክስ ሥርዓት ላይ በበቂ ሁኔታ ኢንቨስት ማድረግ፤ በፖሊሲ እና ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ በሳይንሳዊ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ መረጃን መጠቀም መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል።
ስታቲስቲክስን ለዘላቂ ልማት ማዋል፣ ዘመናዊ የስታቲስቲክስ ተቋማትን መገንባት እንዲሁም የዘርፉን ጥራት፣ ነፃነትና የፈጠራ ውጤቶች ማሳደግ ላይ ሀገራት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል። ኢትዮጵያም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በዘርፉ ያሏትን በጎ ተሞክሮዎች ለማካፈልና በትብብር ለመስራት ቁርጠኝነት እንዳላት አረጋግጠዋል።
በአባዲ ወይናይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: