ኢትዮጵያ በኑክሌር ቴክኖሎጂ መሠረት መጣል የነበረባት ቀደም ብሎ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ተቋማዊ አደረጃጀቱን በጥናት እና በሚጨበጥ ዝግጅት የመገንባት ሥራው ተጠናክሮ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ኑክሌር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቀት በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ የኑክሌር ቴክኖሎጂ አሁን ላይ የጥናት ቡድን ተዋቅሮ፣ ተቋሙ በሕግ ተመሥርቶ፣ መሪዎች እና ባለሙያዎች ተመድበውለት፣ እንዲሁም የቢሮ እና የሰው ሀብት ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ሙሉ ተቋማዊ ቁመና ይዟል።
በጉብኝቱ ወቅትን ያዩት በኤግዚቢሽን የቀረበው የሥራ እንቅስቃሴም ተማሪዎች እና ባለሙያዎች መጥተው በዓይናቸው ሊያዩት የሚችሉት፣ የወረቀት ሐሳብን ወደ ተጨባጭ አቅም የለወጠ እና የዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የሚያሟላ መሆኑን አብራርተዋል።
የኑክሌር ፕሮጀክቱ የሚገነባበትን ቦታ ለማመቻቸት በሙያተኞች ከ30 በላይ ቦታዎች ሲጠኑ የቆዩ ሲሆን፤ የጥናቱ ሂደት ወደ 13፣ በመቀጠል ወደ 5፣ አሁን ደግሞ ደረጃ በደረጃ ተለይተው ወደ 3 ቦታዎች መጠበባቸውን ይፋ አድርገዋል።
እነዚህ የተለዩ ቦታዎች በሀገር ውስጥ ውሳኔ ብቻ ማረጋገጫ እንደማያገኙ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውጭ ተቋማት መጥተው የቦታዎቹን አዋጭነት እና ለቴክኖሎጂው ምቹነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው፣ ያ ሲረጋገጥ ቦታው ተዘጋጅቶ ቴክኖሎጂውን ከሚሰጠው ተቋም ጋር ስምምነት እንደሚፈጸም አስረድተዋል።
ሥራው እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንዴ ኮንትራት ተሰጥቶ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፣ በርካታ ተቋማትን እና ዲፓርትመንቶችን የሚነካ፣ ሰፊ የሰው ሀብት እና ዝግጅት የሚጠይቅ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እና ትልቅ ሕዝብ ያላት በመሆኗ፣ በራስ ላይ ማነስን እና መኮስመንን ማወጅ ትክክል አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዓለም “ደሃ ናችሁ፣ ልካችሁን እወቁ” ቢልም፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛው ትልቅ ሕዝብ ያላት እና 30 ሚሊዮን ተማሪዎች ያሏት ታላቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ዛሬ ያሉት 30 ሚሊዮን ተማሪዎች ከ10 ዓመት በኋላ የተፈጥሮ ሀብቷን አውጥተው ከፍተኛ ሀብት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ለዚህ ደግሞ ልጆቹ ቦታው ላይ ሲደርሱ ከመጠበቅ ይልቅ አሁኑኑ መሠረቱን እና አስቻይ ሁኔታውን አዘጋጅቶ ማቆየት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ነገ ዓለም በሚወዳደርባቸው በኑክሌር፣ በስፔስ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መስኮች ዝግጁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
ምንም እንኳን ሀገራችን በነዚህ መሠረታዊ እውቀቶች ላይ ዘግይታ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ባለችበት ተቋማዊ ቁመና እና አቅጣጫ የሚኮራ እና ለልጆቻችን አስተማማኝ መሠረት የሚያስቀምጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: