Search

ኢትዮጵያ 2 ሺህ 400 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የኑክሌር ፕሮጀክት ልትገነባ ነው

ረቡዕ ጥቅምት 11, 2019 60

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት ውስጥ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ዩኒቶችን ለመገንባት ማቀዷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ይህ በድምሩ 2 ሺህ 400 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ፕሮጀክት፣ እንደ ውኃ፣ ፀሐይ እና ነፋስ ኃይል በወቅቶች መፈራረቅ አቅሙ የማይዋዥቅ በመሆኑ፣ ዓመቱን ሙሉ ወጥ በሆነ አቅም በሚያመርተው የኃይል መጠን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደሚበልጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ለኑክሌር ኃይል ማመንጫው ግንባታ በባለሙያዎች ከተጠኑ ከ30 በላይ ቦታዎች መካከል በሒደት ተጣርተው ሦስት ቦታዎች መለየታቸው ተገልጿል። እነዚህ የተለዩ ቦታዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት አዋጭነታቸው እና ምቹነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ ቴክኖሎጂውን ከሚያቀርቡ አካላት ጋር ስምምነት በመፈጸምና የሰው ኃይል በማዘጋጀት ወደ ተግባራዊ ግንባታ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የኑክሌር ኢንቨስትመንት የመጀመሪያ ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም፣ አንዴ ከተገነባ ከ60 እስከ 100 ዓመታት የሚዘልቅ እና ለትውልድ የሚተርፍ ትሩፋት ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገለጹት።

የኑክሌር ኢነርጂ ልማቱ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ መነቃቃት በማፋጠን እና ንጹሕ የኃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ ረገድ የጀርባ አጥንት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በቂ የኃይል አቅርቦት የሌለው ሀገር ዘላቂ ዕድገት ሊያረጋግጥ እንደማይችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በኃይል ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለውጭ ገበያ በመሸጥ እና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ የኢኮኖሚ አቅሟን እንደሚያሳድግ አብራርተዋል።

ከኑክሌር ልማቱ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሌሎች ግዙፍ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች በፈጣን ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቅሷል።

በዚህም መሠረት የአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሦስት እና አራት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ እንደሚሸጋገር፣ የተፈጥሮ ጋዝ ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተመርቆ ሁለተኛው መጀመሩ፣ እንዲሁም ከወደብ እስከ ማዳበሪያ ፋብሪካ የሚዘረጋው የቧንቧ መስመር እና ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሞርጌጅ ባንክ የማቋቋም ጥናት መጠናቀቁ ሀገራዊ ስኬት መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: