በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አንዲት እድሜዋ 40 ዓመት ከሆናት እናት ማህፀን ውስጥ 19 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ በስኬት በተካሄደ ቀዶ ህክምና መወገዱ ተገለጸ።
የህክምና ሂደቱን የመሩት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የማህፀን ካንሰር ሰብ-ስፔሻሊስት ዶክተር ታደሰ ኡርጌ ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ህመምተኛዋ የአራት ልጆች እናት ስትሆን ለሰባት ወራት ያህል የሆድ መነፋት ምልክት ይታይባት ነበር ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ታደሰ ገለጻ ህመሙ «ኦቬሪያን ሲስት» (Ovarian Cyst) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሴቶች የመራቢያ አካል ክፍል የሚነሳ የእጢ አይነት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የህመሙ ትክክለኛ መነሻ ምክንያት በእርግጠኝነት አይታወቅም ያሉት ዶክተሩ፤ ነገር ግን በኦቫሪ ህዋሳት የመራባት ሂደት ወቅት በሚፈጠር የዘረመል እክል ምክንያት ጤናማ ያልሆኑ ህዋሳት እንደሚፈጠር ነው የጠቆሙት።
እነዚህ ህዋሳት በጊዜ ሂደት እየተባዙ በመሄድ ትልቅ እጢ ሊፈጥሩ እንደሚችሉም እና እጢው የካንሰርነት ባህሪ ያለው ሊሆን የሚችል ሲሆን፤ ይህም ከወጣ በኋላ በሚደረግ የላቦራቶሪ ምርምር የሚረጋገጥ ይሆናል ብለዋል።
እንደነዚህ አይነት ትላልቅ እጢዎች ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጳውሎስም ሆነ በሌሎች የሃገራችን ሆስፒታሎች ተከስተው የሚያውቁና በቀዶ ጥገና የተወገዱበት አጋጣሚ ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።
በተለይም እድሜያቸው ገፋ ያሉ እናቶች ላይ በብዛት ሊታይ የሚችል ሲሆን፤ አንዳንዴ ምንም አይነት ቅድመ-ምልክት የማያሳዩ በመሆናቸው እጢው በጣም ትልቅ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ሊታወቅ እንደሚችል አንስተዋል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: