Search

የድል ሠራዊት፦ የ119 ዓመታት የተቋም ጽናትና የራስ አቅም ልዕልና

ሓሙስ ጥቅምት 12, 2019 67

በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ ግዙፍ ወታደራዊ ፋብሪካዎችን ገንብቶ ወደ ምርት መግባት፣ የሀገር ውስጥ የትጥቅ ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ መሸፈን፤ ይህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለዓለም እያሳየ ያለው አዲስና ተጨባጭ እውነታ ነው።

ለዘመናት የውጭ የጦር መሣሪያ አምራቾች ጥገኛ የነበረው የሀገራችን የመከላከያ ዘርፍ፣ ዛሬ ላይ ያንን የጥገኝነት ታሪክ ሙሉ በሙሉ ሽሮ በራስ ልጆች ጥበብና አቅም የቆመ ግዙፍ የኢንዱስትሪ አቅም ፈጥሯል።

ይህ የመከላከያ ኢንዱስትሪው ፈጣን ዕመርታ በድንገት የተፈጠረ ሳይሆን ሠራዊቱ እንደ ዘመናዊ ተቋም ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ያካበተው የተቋማዊ ጽናትና የሪፎርም ውጤት ነው።

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብ ፈተናዎች ወደ መልካም አጋጣሚ በምትቀይርበት በዚህ ወቅት፣ የድል ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ሥነ-ልቦና፣ በዘመነ አደረጃጀትና በቴክኖሎጂ ዝግጁነት ተገንብቷል።

ይህም ኢትዮጵያ ከተፈጥሯዊና ታሪካዊ ታላቅነቷ ጋር የሚመጣጠን፣ ማንም በቀላሉ ሊደፍራት የማይችል ራስን በራስ የመከላከል ፅኑ መሠረት ላይ መቆሟን በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ይሁንና የዚህን የ119 ዓመት ባለታሪክ ተቋም ጥንካሬ የሚወስነው የታጠቀው ዘመናዊ መሣሪያና የገነባው ፋብሪካ ብቻ አይደለም። ሠራዊቱ ከማንኛውም ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ፣ በሀገራዊ ፍቅርና አንድነት ላይ መገንባቱ የማይሸነፍበት ዋነኛ ምስጢር ነው።

በዚህም የሀገራችንን ሉዓላዊነት በመዳፈርና የውስጥ ሰላሟን ለማደፍረስ የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን የከፈቱብንን ጦርነቶች በመመከት ሀገርን  ለዚህ ትውልድ ያስረከቡን የየዘመኑ ጀግኖች የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ባለውለታዎች ናቸው።

የአሁኑ ትውልድ ሠራዊትም ይህንኑ የቀደምት አባቶቹን የጀግንነት አደራ ከዘመኑ ወታደራዊ ሳይንስ ጋር አዋህዶ የሀገራችንን ሉዓላዊነት በፅኑ አለት ላይ አቁሞታል።

ይህ የድል ሠራዊት ጠላትን የሚያርድ ክንደ ብርቱ፣ በፈተና እሳት ተፈትኖ የነጠረ እጅግ ጀግና እና ለሀገሩ ክብር ሁልጊዜም በተጠንቀቅ የቆመ ንቁ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።

የኢትዮጵያ ዳር ድንበር እንዳይደፈርና የሕዝቧ ሰላም እንዳይደፈርስ፣ ውድ ሕይወቱንና ደሙን ያለ አንዳች ስስት የሚገብር የሉዓላዊነታችን ቋሚ ጋሻና መከታ ነው።

በዱር በገደሉ፣ በሐሩርና በቁሩ ሳይበገር ለሀገሩ ሉዓላዊነት መስዋዕትነትን እንደ ክብር ጌጥ የተቀበለው ይህ ጀግና ሠራዊት፣ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ እንድትጓዝ ያስቻለ የኩራታችን ምንጭ ነው።

በመከላከያው ዘርፍ የታየው ይህ የአምራችነትና የቴክኖሎጂ አብዮት፣ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎችም ኢኮኖሚያዊ መስኮች ከጀመረችው ሁለንተናዊ የማንሰራራት ጉዞ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።

በራስ አቅም የሀገርን ፍላጎት የማሟላት ስኬት በሠራዊቱ የኢንዱስትሪ ተቋማት በተጨባጭ መታየቱ፣ ሀገራችን ልጆቿን የምታኮራበትና ብሩህ ርዕይዋን እውን የምታደርግበት አዲስ ዘመን መሆኑን ያሳያል።

 የ119 ዓመቱ የድል ሠራዊት የደረሰበት ይህ አስተማማኝ የመከላከል፣ የማምረትና የጀግንነት ከፍታ በዚህ ሳይገታ ለላቀ ሀገራዊ ክብርና ልዕልና ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

 

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: