የፌደራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጉራጌ ዞን የተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎች ላይ አጠቃላይ የመስክ ምልከታ እያደረጉ ይገኛሉ።
በዛሬው የመስክ ጉብኝት በቸሀ እና በእኖር ወረዳዎች በክላስተርና በኩታገጠም እርሻ የለሙ ሰብሎች የተጎበኙ ሲሆን፣ በዞኑ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች ለሀገራዊ የግብርና ሽግግር ማሳያ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በዞኑ በመኸር ወቅት ጤፍ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎችን በክላስተር በማልማት የአምራችነት አቅምን ለማሳደግ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም 30 ሺህ ሄክታር መሬት በጤፍ የተሸፈነ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 25 ሺህ ሄክታሩ በክላስተር የለማ ነው።
በተመሳሳይም ከበቆሎ ልማት ማሳዎች ውስጥ 44 ሺህ ሄክታሩ በክላስተር መሸፈኑ ተገልጿል። በቸሀ ወረዳም 8 ሺህ 41 ሄክታር መሬት በጤፍ፣ 2 ሺህ 122 ሄክታር መሬት በኩታገጠም እርሻ ለምቷል።
በተቀናጀ ግብርና፣ በመስኖ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሳትፎ የግብርናውን ዘርፍ ወደ ዘመናዊና ተወዳዳሪነት ለማሸጋገር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በጉብኝቱ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም፣ የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ፣ የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዲሁም የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ይህ በጉራጌ ዞን የሚታየው ዘመናዊ የግብርና እንቅስቃሴና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አርአያነት፣ ሀገራችን በምግብ ራስን ለመቻል የቆመች #ትልቅሀገር፣ በትጋት የሚያመርት #ትልቅሕዝብ እና ወደ ላቀ ኢኮኖሚያዊ ከፍታ የሚያሸጋግር #ታላቅርዕይ ያላት መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: