የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት አራት ዓመታት ከስምንት ወራት በቆየው የስራ ጊዜው የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በስኬት ማጠናቀቁን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
ዋና ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ በሀገራችን የሚታዩ የተለያዩ የሐሳብ ልዩነቶች ወደ ውይይት እንዲመጡ የማድረግና አካታች የምክክር መድረኮችን የመፍጠር ስራ በብቃት ማከናወኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ሂደት ለማጠቃለያ ጉባኤው የቀረቡ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ተለይተው ከአንድ ወር በላይ ውጤታማ ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን፣ በውይይቶቹ ማጠቃለያ የተዘጋጁ 394 ምክረ ሐሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረባቸውን አብራርተዋል።
በሂደቱ የተገኙ ልምዶችን በተመለከተ ፕሮፌሰር መስፍን ሲያብራሩ፣ ከሁሉም አካላት የቀረቡ ሐሳቦች ላይ በመወያየት መቀራረብ እንደሚቻል በተግባር መታየቱን ገልጸዋል።
ይህ አካታች የውይይት ሂደት ለዘመናት በዘለቁ ውስብስብ ሀገራዊ ችግሮች ላይ በግልጽ በመነጋገር ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለሰላማዊ የፖለቲካ አካሄድ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም አብራርተዋል። ይህም ለወደፊቱ ሀገራዊ የመወያየትና የመደመጥ ባህል ጠንካራ መሠረት የጣለ ትልቅ ስኬት መሆኑን አሳውቀዋል።
ምንም እንኳን ጥቅምት 14 ቀን የኮሚሽኑ የስራ ዘመን በይፋ የሚያበቃ ቢሆንም በቀጣይ ሂደቶችም ሀገራዊ ምክክሩ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ፋይዳ ያገኝ ዘንድ አጀንዳዎችን ለምክር ቤቱ ከማስረከብ ባለፈ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል። በተጨማሪም ቀሪ የጽሕፈት ቤት ስራዎችን እና የሰነድ ርክክቦችን የማጠናቀቅ ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማነትና ለተከናወኑት ስራዎች ሙሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ሁሉ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
ዘሃራ መሃመድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: