Search

ከኮሪደር ልማት እስከ ገጠር ሽግግር፤ የኢትዮጵያ አዲሱ የልማት ሪፎርም

ሓሙስ ጥቅምት 12, 2019 48

የጥንታዊ ስልጣኔ፣ የታሪካዊ ክብር እና የኪነ ህንፃ ምጥቀት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የትናንቱን የአክሱም፣ የላሊበላ እና የጀጎል ግንብ ጥበብ ከነገው የብልፅግና ተስፋ ጋር በማስተሳሰር የታሪክ አሻራዋን የሚያሳርፉ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተጨባጭ እያረጋገጠች ትገኛለች።

የዚህ ሀገራዊ እይታ አካል የሆነው አዲስ የልማት ሪፎርም፣ በከተሞች የተመዘገበውን ውጤታማ የኮሪደር ልማት ስኬት ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ በማስፋፋት ላይ ይገኛል፤ ይህም የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር እና በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን የእድገት ልዩነት ለማጠበብ ዘላቂ መሰረት በመጣል ላይ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተቀረፀው ይህ የገጠር ኮሪደር ልማትና የሽግግር ስትራቴጂ መሰረተ ልማትን ከማዘመን ባለፈ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው።

ልማቱ የገጠር ነዋሪዎችን ከተበታተነ አሰፋፈር ወደ ተቀናጁ የገጠር መንደሮች በማምጣት ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃን፣ ኤሌክትሪክና የፀሐይ ብርሃን መብራቶችን እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው።

ይህም ቀደም ሲል ለረጅም ሰዓታት በእግር ይጓዙ የነበሩ እናቶችን እና ህፃናትን እንግልት የቀነሰ ሲሆን፣ የገጠሩን የምሽት ገፅታም በከፍተኛ ሁኔታ ቀይሮታል።

በአነስተኛ ወጪ በአካባቢ ግብዓቶች የሚገነቡ ሞዴል መኖሪያ ቤቶችን፣ ዘመናዊ የእንስሳት ማደሪያዎችን፣ የባዮ ጋዝ አቅርቦትን፣ የፍራፍሬና የጓሮ አትክልት ልማትን ከንብ፣ እንቁላል፣ ወተትና ስጋ ምርት ጋር በማቀናጀት የአርሶ አደሩ ገቢና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እንዲያድግ አድርጓል።

በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌማት ትሩፋት የተገኙ ውጤቶችን በማስተሳሰር የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት አካባቢውን ለቱሪዝምና ለስራ እድል ፈጠራ ማዕከልነት እያሸጋገረው ይገኛል።

ይህ የገጠር ሽግግር የግብርናውን ዘርፍ ከባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ ምርታማነት የሚያሸጋግር ሲሆን፣ በስንዴ ምርታማነት ላይ የተመዘገበው አመርቂ ውጤት የዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

በገጠር መንደሮች አቅራቢያ የሚስፋፉ የአግሮ ኢንዱስትሪ ማዕከላት ምርቶች ላይ እሴት እንዲደመርባቸው በማድረግ የትራንስፖርት ወጪን ከመቀነሳቸውም በላይ ራሳቸውን የቻሉ አዳዲስ የገጠር ከተሞች እንዲፈጠሩ መንገድ ከፍተዋል።

እነዚህ ታዳጊ ከተሞች ጠንካራ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ገጠሩ የግብርና ምርቶችን ለከተማ፣ ከተማው ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርቶችንና ቴክኖሎጂዎችን ለገጠር የሚያቀርብበትን የጋራ መደጋገፍ አጠናክረውታል።

በአጠቃላይ በገጠር የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችና ከግብርና ውጭ ያሉ በርካታ የስራ እድሎች መፈጠራቸው ወጣቶች ወደ ትልልቅ ከተሞች የሚያደርጉትን ፍልሰት በመቀነስ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

እንዲሁም የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ከማረጋገጥ ባለፈ "እኛ አንችልም" የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በመስበር በራስ አቅም የመልማት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ በመሆኑ ይህንን የትውልድ ፕሮጀክት ስኬታማ ለማድረግ የተቀናጀ ቁርጠኝነት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በብሌን ደምበሎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: