Search

"የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የሚወስኑ ሕጎችን በመቅረፅ አፍሪካ ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት ይገባል"፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 14, 2019 59

ዓለም አቀፍ ጫናዎች እና የጂኦፖለቲካ ሽግግሮች በዜጎች ዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩና አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋን የሚወስኑ ደንቦችን በማውጣት ረገድ ጠንካራና አንድ ወጥ ድምፅ ሊኖራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው 12ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፣ አፍሪካውያን የሚጠበቅባቸውን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የሰላም ግንባታ ማረጋገጥ የሚችሉት የውጭ ጫናዎችን ብቻቸውን በመቆጣጠር ሳይሆን የጋራ ጽናትን በመፍጠር እና የወደፊት የጋራ ሕጎቻችንን በራሳችን ድምፅ በመቅረጽ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የግልም የጋራም ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዋናው የአህጉሪቱ ቀዳሚ ግብ ዜጎችን መጠበቅ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስከበር መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ሁልጊዜም ለሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት በሮች ክፍት መሆናቸውን በመግለጽ ሰላምን የሚመርጡ አካላትን ለመቀበል ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

ሰላም በስምምነት ብቻ ሳይሆን በተግባር ሲተረጎም እና ሕዝቡ ተጠቃሚ ሲሆን የጸና እንደሚሆን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ያጠናቀቃቸው እና ለፓርላማ እና ለክልል መንግሥታት ያደረሳቸው ምክረ ሀሳቦች አሁን ወደ ተግባር ሊለወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሕዝብ ዘንድ ተቋማዊ እምነትን መገንባት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ እና ማኅበራዊ ኑሮን ማሻሻል ለሰላም ዘላቂነት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በብሌን ደምበሎ

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: